ዘሌዋውያን 23 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘሌዋውያን 23:1-44

1እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምትዋጇቸው የተመረጡ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት እነዚህ ናቸው፤

ሰንበት

3“ ‘ሥራ የምትሠሩበት ስድስት ቀን አላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት፣ የተቀደሰ ጉባኤ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ስለሆነ፣ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩበት።

የፋሲካና የቂጣ በዓል

23፥4-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20ዘኍ 28፥16-25ዘዳ 16፥1-8

4“ ‘የተመረጡ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት ብላችሁ በተወሰኑላቸው ጊዜያት የምታውጇቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እነዚህ ናቸው፤ 5የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይጀመራል። 6በዚያው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ሰባት ቀንም ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ። 7በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዕለት ተግባራችሁንም አታከናውኑ። 8ሰባት ቀን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ በዚያ ዕለት የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑ።’ ”

የበኵራት ስጦታ በዓል

9እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ከሰበሰባችሁት እህል የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ አቅርቡ፤ 11ነዶው ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዘው፤ ካህኑ ነዶውን የሚወዘውዘው በሰንበት ቀን ማግስት ነው። 12ነዶውን በምትወዘውዙበት ቀን እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ 13ከዚህም ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ሁለት ዐሥረኛ የኢፍ23፥13 4.5 ሊትር ገደማ ይሆናል፤ እንዲሁም 17 ይመ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ለእህል ቍርባን፣ አንድ አራተኛ የኢን23፥13 1 ሊትር ገደማ ይሆናል መስፈሪያ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን አቅርቡ። 14ስጦታውን ለአምላካችሁ (ኤሎሂም) እስከምታቀርቡበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ እንጀራም ቢሆን ቈሎ ወይም እሸት አትብሉ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።

የመከር በዓል

23፥15-22 ተጓ ምብ – ዘኍ 28፥26-31ዘዳ 16፥9-12

15“ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቍጠሩ። 16እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ። 17በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምጡ። 18ከእንጀራውም ጋር ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። 19እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት23፥19 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል አቅርቡ። 20ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋር የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው። 21በዚያኑ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።

22“ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”

የመለከት በዓል

23፥23-25 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥1-6

23እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በመለከት ድምፅም የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ። 25መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ”

የስርየት ቀን

23፥26-32 ተጓ ምብ – ዘሌ 16፥2-34ዘኍ 29፥7-11

26እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 27“የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤23፥27 ወይም ጹሙ፤ እንዲሁም 29፡32 ይመ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ። 28በእግዚአብሔር (ያህዌ) በአምላካችሁ (ኤሎሂም) ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ። 29በዚያ ዕለት ሰውነቱን የሚያጐሳቍል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 30በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 31ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው። 32ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ23፥32 ወይም ጹሙ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።”

የዳስ በዓል

23፥33-43 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥12-39ዘዳ 16፥13-17

33እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 34“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቈያል። 35የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት። 36ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት።

37“ ‘የሚቃጠል መሥዋዕትንና የእህል ቍርባንን፣ መሥዋዕትንና የመጠጥ ቍርባንን በተመደበላቸው ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ለማቅረብ፣ የተቀደሱ ጉባኤዎችን የምታውጁባቸው የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት እነዚህ ናቸው። 38እነዚህ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ከምታቀርቡት፣ ከስጦታችሁ፣23፥38 ወይም እነዚህ በዓላት ከእግዚአብሔር ሰንበታት በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ናቸው፤ ስጦታዎቹም ከስእለታችሁና ከበጎ ፈቃድ ስጦታችሁ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ስጦታዎች ናቸው።

39“ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል። 40በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ። 41በየዓመቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት። 42ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤ 43በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”

44በዚህ ሁኔታም ሙሴ የተመረጡትን የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ።