ኤርምያስ 51 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 51:1-64

1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ በባቢሎንና51፥1 ሌብ ካማይ የከላውዴዎን ማለትም የባቢሎን ስም ነው። በምድሯ ላይ፣

የሚያጠፋ ነፋስ አስነሣለሁ።

2እንዲያበጥሯትና እንዲያወድሟት፣

ባዕዳንን በባቢሎን ላይ እልካለሁ፤

በመከራዋም ቀን፣

ከብበው ያስጨንቋታል።

3ቀስተኛው ቀስቱን እስኪገትር፣

የጦር ልብሱንም እስኪለብስ ፋታ አትስጡት፤

ለወጣቶቿ አትዘኑ፤

ሰራዊቷንም ፈጽማችሁ አጥፉ።51፥3 አጥፉ ለሚለው የዕብራይስጡ ቃል የሚያመለክተው ነገሮችን ወይም ሰዎችን ዳግም ላይመለሱ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መስጠት ነው።

4በባቢሎን51፥4 ወይም ከላውዴዎን ምድር ታርደው፣

በአደባባዮቿም እስከ ሞት ቈስለው ይወድቃሉ።

5ምድራቸው51፥5 ወይም የባቢሎናውያን ምድር በእስራኤል ቅዱስ ፊት፣

በበደል የተሞላች ብትሆንም፣

እስራኤልንና ይሁዳን አምላካቸው

የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር አልጣላቸውም።

6“ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡ!

ፈጥናችሁም ሕይወታችሁን አትርፉ!

በኀጢአቷ ምክንያት አትጥፉ።

የእግዚአብሔር የበቀል ጊዜ ነው፤

እርሱም የሥራዋን ይከፍላታል።

7ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ የወርቅ ጽዋ ነበረች፤

ምድርንም ሁሉ አሰከረች።

ሕዝቦች ከወይን ጠጇ ጠጡ፤

ስለዚህ አሁን አብደዋል።

8ባቢሎን በድንገት ወድቃ ትሰበራለች፤

ዋይ በሉላት!

ምናልባት ልትፈወስ ስለምትችል፣

ለቍስሏ የሚቀባ መድኀኒት ፈልጉላት።

9“ ‘ባቢሎንን ለመፈወስ ሞክረን ነበር፤

እርሷ ግን ልትፈወስ አትችልም፤

ፍርዷ እስከ ሰማይ ስለ ደረሰ፣

እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ስላለ፣

ትተናት ወደየአገራችን እንሂድ።’

10“ ‘እግዚአብሔር ቅንነታችንን መሰከረ፤

ኑ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ያደረገውን፣

በጽዮን እንናገር።’

11“ፍላጾችን ሳሉ፤

ጋሻዎችን አዘጋጁ፤

የእግዚአብሔር ሐሳብ ባቢሎንን ለማጥፋት ስለሆነ፣

የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቷል፤

እግዚአብሔር ይበቀላል፤

ስለ ቤተ መቅደሱ ይበቀላል።

12በባቢሎን ቅጥር ላይ ዐላማ አንሡ

ጥበቃውን አጠናክሩ፤

ዘብ ጠባቂዎችን አቁሙ፤

ደፈጣ ተዋጊዎችን አዘጋጁ

እግዚአብሔር በባቢሎን ሕዝብ ላይ የወሰነውን፣

ዐላማውን ያከናውናል።

13አንቺ በብዙ ውሃ አጠገብ የምትኖሪ፣

በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፤

የምትወገጂበት ጊዜ ወጥቷል፤

ፍጻሜሽ ደርሷል።

14የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሏል፤

ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሰራዊት ያጥለቀልቅሻል፤

እነርሱም በድል አድራጊነት በላይሽ ያቅራራሉ።

15“ምድርን በኀይሉ የሠራ፣

ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፣

ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

16ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤

ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤

መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤

ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

17“እያንዳንዱ ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው፤

የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው በጣዖቱ ዐፍሯል፤

የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤

እስትንፋስ የላቸውም።

18እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፣

ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።

19የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደ እነዚህ አይደለም፤

እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤

እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።

ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

20“አንቺ የእኔ ቈመጥ፣

የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤

በአንቺ ሕዝቦችን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ መንግሥታትን አጠፋለሁ፤

21በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ ሠረገላውንና ሠረገላ ነጂውን እሰባብራለሁ፤

22በአንቺ ወንዱንና ሴቱን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ ሽማግሌውንና ወጣቱን እሰባብራለሁ።

በአንቺ ጐረምሳውንና ኰረዳዪቱን እሰባብራለሁ።

23በአንቺ እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፣

በአንቺ ገበሬውንና በሬውን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ ገዦችንና ባለሥልጣኖችን እሰባብራለሁ።

24“በጽዮን ላይ ስላደረሱት ጥፋት ሁሉ ለባቢሎንና በባቢሎን51፥24 ወይም ከላውዴዎን፤ 35 ይመ። ለሚኖሩት ሁሉ ዐይናችሁ እያየ ዋጋቸውን እከፍላቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር

25“አንቺ ምድርን ሁሉ ያጠፋሽ፣

አጥፊ ተራራ ሆይ፤ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣”

ይላል እግዚአብሔር

“እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤

ከገመገም ቍልቍል አንከባልልሻለሁ፤

የተቃጠለም ተራራ አደርግሻለሁ።

26ከአንቺ ለማእዘን የሚሆን ድንጋይ፣

ለመሠረትም የሚሆን ዐለት አይወሰድም፤

ለዘላለም ባድማ ትሆኛለሽ፤”

ይላል እግዚአብሔር

27“በምድር ሁሉ ላይ ሰንደቅ ዐላማ አንሡ!

በሕዝቦች መካከል መለከትን ንፉ!

ሕዝቦችን ለጦርነት በእርሷ ላይ አዘጋጁ፤

የአራራትን፣ የሚኒንና የአስከናዝን መንግሥታት፣

ጠርታችሁ በእርሷ ሰብስቧቸው፤

የጦር አዝማች ሹሙባት፤

ፈረሶችንም እንደ አንበጣ መንጋ ስደዱባት።

28የሜዶንን ነገሥታት፣

ገዦቿንና ባለሥልጣኖቿን ሁሉ፣

በግዛታቸው ሥር ያሉትን አገሮች ሁሉ፣

እነዚህን ሕዝቦች ለጦርነት አዘጋጁባት።

29ሰው በዚያ መኖር እስከማይችል ድረስ፣

የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ፣

እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ ያቀደው ስለሚጸና፣

ምድር ትናወጣለች፤ በሥቃይም ትወራጫለች።

30የባቢሎን ጦረኞች መዋጋት ትተዋል፤

በምሽጎቻቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፤

ኀይላቸው ተሟጥጧል፤

እንደ ሴት ሆነዋል፤

በማደሪያዎቿም እሳት ተለኵሷል፤

የደጇም መወርወሪያ ተሰብሯል።

31ከተማዪቱ ሙሉ በሙሉ መያዟን፣

ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር፣

አንዱ ወሬኛ ሌላውን ወሬኛ፣

አንዱ መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ወዲያው ወዲያው ይከተላል፤

32መልካዎቿ እንደ ተያዙ፣

የወንዝ ዳር ምሽጎቿ እንደ ተቃጠሉ፣

ወታደሮቿም እንደ ተደናገጡ ሊነግሩት ይሯሯጣሉ።”

33የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ፣

የእህል መውቂያ አውድማ ናት፤

የመከር ወራቷም ፈጥኖ ይደርስባታል።”

34“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላን፣

አድቅቆ ፈጨን፤

እንደ ባዶ ማድጋ አደረገን፤

እንደ ዘንዶ ዋጠን፣

እንደ ጣፋጭ በልቶን ሆዱን ሞላ፤

በኋላም አንቅሮ ተፋን፤

35የጽዮን ነዋሪዎች፣ እንዲህ ይላሉ፤

በሥጋችን51፥35 ወይም በእኛና በልጃችን ላይ የተፈጸመው ላይ የተፈጸመው ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን፤”

ኢየሩሳሌም እንዲህ ትላለች፤

“ደማችን በባቢሎን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን።”

36ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ እሟገትልሻለሁ፣

በቀልሽንም እኔ እበቀልልሻለሁ፤

ባሕሯን አደርቃለሁ፣

የምንጮቿንም ውሃ።

37ባቢሎን የፍርስራሽ ክምር፣

የቀበሮዎች መፈንጫ፣

የድንጋጤና የመሣለቂያ ምልክት ትሆናለች፤

የሚኖርባትም አይገኝም።

38ሕዝቦቿ ሁሉ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤

እንደ አንበሳ ግልገልም ያጕረመርማሉ።

ጕረሯቸው በደረቀ ጊዜ

ድግስ አዘጋጅላቸዋለሁ፤

እንዲሰክሩም አደርጋቸውና

39በሣቅ እየፈነደቁ፣

ለዘላለም ላይነቁ ይተኛሉ።”

ይላል እግዚአብሔር

40“እንደ ጠቦት፣

እንደ አውራ በግና እንደ ፍየል፣

ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።

41“ሼሻክ51፥41 ሼሻክ የባቢሎን ስውር ስም ነው። እንዴት ተማረከች!

የምድር ሁሉ ትምክሕትስ እንዴት ተያዘች!

ባቢሎን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ፣

ምንኛ አስደንጋጭ ሆነች።

42ባሕር በባቢሎን ላይ ይወጣል፤

ሞገዱም እየተመመ ይሸፍናታል።

43ከተሞቿ ሰው የማይኖርባቸው፣

ዝርም የማይልባቸው፣

ደረቅና በረሓማ ቦታ፣

ባድማ ምድርም ይሆናሉ።

44ቤልን በባቢሎን ውስጥ እቀጣለሁ፤

የዋጠውን አስተፋዋለሁ፤

ሕዝቦች ከእንግዲህ ወደ እርሱ አይጐርፉም፤

የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።

45“ሕዝቤ ሆይ፤ ከመካከሏ ውጡ!

ሕይወታችሁን አትርፉ!

ከአስፈሪው የእግዚአብሔር ቍጣ አምልጡ።

46ወሬ በምድሪቱ ሲሰማ፣

ተስፋ አትቍረጡ፤ አትፍሩም፤

ገዥ በገዥ ላይ ስለ መነሣቱ፣

ዐመፅም በምድሪቱ ስለ መኖሩ፣

አንድ ወሬ ዘንድሮ፣ ሌላውም ለከርሞ ይመጣል፤

47የባቢሎንን ጣዖታት የምቀጣበት ጊዜ፣

በርግጥ ይመጣልና።

ምድሯ በሙሉ ትዋረዳለች፤

የታረዱትም በሙሉ በውስጧ ይወድቃሉ።

48ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ፣

በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፤

አጥፊዎች ከሰሜን ወጥተው፣

እርሷን ይወጓታልና፤”

ይላል እግዚአብሔር

49“በምድር ሁሉ የታረዱት፣

በባቢሎን ምክንያት እንደ ወደቁ፣

ባቢሎንም በእስራኤል በታረዱት ምክንያት መውደቅ ይገባታል።

50ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፤

ሂዱ! ጊዜ አትፍጁ፤

በሩቅ ምድር ያላችሁ እግዚአብሔርን አስታውሱ፤

ኢየሩሳሌምንም አስቧት።”

51“ባዕዳን ሰዎች ወደ ተቀደሰው፣

ወደ እግዚአብሔር ቤት ስለ ገቡ፣

እኛ ተሰድበናል፤

ዕፍረትም ፊታችንን ሸፍኗል፤

ውርደትም ተከናንበናል።”

52“እንግዲህ ጣዖቶቿን የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፤”

ይላል እግዚአብሔር

“በምድሯም ሁሉ፤

ቍስለኞች ያቃስታሉ።

53ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣም፣

ከፍ ያለ ምሽጓን ብታጠናክርም፣

አጥፊዎች እሰድድባታለሁ፤”

ይላል እግዚአብሔር

54“ከባቢሎን ጩኸት፣

ከባቢሎናውያንም51፥54 ወይም ከለዳውያን ምድር፣

የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል።

55እግዚአብሔር ባቢሎንን ያጠፋታል፤

ታላቅ ጩኸቷንም ጸጥ ያደርጋል።

ሞገዳቸው እንደ ታላቅ ውሃ ይተምማል፤

ጩኸታቸውም ያስተጋባል።

56በባቢሎን ላይ አጥፊ ይመጣል፤

ጦረኞቿ ይማረካሉ፤

ቀስታቸውም ይሰበራል፤

እግዚአብሔር ግፍን የሚበቀል፣

ተገቢውንም ሁሉ የሚከፍል አምላክ ነውና።

57ባለሥልጣኖቿንና ጥበበኞቿን፣

ገዦቿንና መኳንንቷን፣ ጦረኞቿንም አሰክራለሁ፤

ለዘላለም ይተኛሉ፤ አይነቁምም፤”

ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ

እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ።

58የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ወፍራሙ የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤

ከፍ ያሉት ደጆቿም በእሳት ይቃጠላሉ፤

ሰዎቹ በከንቱ ይደክማሉ፤

የሕዝቡም ልፋት ለእሳት ይሆናል።”

59የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የንጉሡ የግቢ አስከልካይ የነበረው የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ ከንጉሡ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ የሰጠው መልእክት ይህ ነው። 60ኤርምያስ ስለ ባቢሎን ጽፎ ያስቀመጠውን ሁሉ፣ በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ጥፋት ሁሉ በብራና ጥቅልል ላይ ጻፈው። 61ለሠራያም እንዲህ አለው፤ “ባቢሎን በደረስህ ጊዜ፣ ይህን ቃል ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማንበብ አትዘንጋ። 62እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህችን ስፍራ ሰውም ሆነ እንስሳ እስከማይኖርባት ድረስ ለዘላለም ባድማ አደርጋታለሁ ብለሃል።’ 63ይህን ብራና አንብበህ ከጨረስህ በኋላ፣ ድንጋይ አስረህበት ኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ ጣለው፤ 64እንዲህም በል፤ ‘ባቢሎንም እኔ ከማመጣባት ጥፋት የተነሣ፣ እንደዚሁ ትሰጥማለች፤ ከእንግዲህም አትነሣም፤ ሕዝቧም ይወድቃል።’ ”