ኤርምያስ 26 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 26:1-24

በኤርምያስ ላይ የግድያ ዛቻ

1በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ፣ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣ፤ 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ቆመህ፣ ለማምለክ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከይሁዳ ከተሞች ለሚመጣው ሕዝብ ሁሉ ተናገር፤ አንዲትም ቃል ሳታስቀር የማዝዝህን ሁሉ ንገራቸው። 3ምናልባትም ሰምተው እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስላደረጉት ክፋት ላመጣባቸው ያሰብሁትን ቅጣት እተዋለሁ። 4እንዲህም በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ባትሰሙኝና የሰጠኋችሁን ሕጌን ባትጠብቁ፣ 5ልትሰሟቸው ይገባ የነበረውን ወደ እናንተ ደጋግሜ የላክኋቸውን የአገልጋዮቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፣ 6ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርጋለሁ፤ ይህችንም ከተማ በምድር ሕዝብ ሁሉ ፊት የተረገመች አደርጋታለሁ።’ ”

7ኤርምያስ ይህን ቃል በእግዚአብሔር ቤት ሲናገር፣ ካህናቱና ነቢያቱ፣ ሕዝቡም ሁሉ ሰሙ። 8ነገር ግን ኤርምያስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ያዘዘውን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣ ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡም ሁሉ ይዘውት እንዲህ አሉ፤ “አንተ መገደል አለብህ! 9ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይህችም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ በእግዚአብሔር ስም ለምን ትንቢት ትናገራለህ?” ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተሰብስበው ኤርምያስን ከበቡት።

10የይሁዳም ባለሥልጣኖች ስለ እነዚህ ነገሮች በሰሙ ጊዜ፣ ከቤተ መንግሥት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔር ቤት፣ አዲሱ በር በተባለው መግቢያ ተቀመጡ። 11ካህናቱና ነቢያቱም ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ፣ “በጆሯችሁ እንደ ሰማችሁት ይህ ሰው በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ስለ ተናገረ ሞት ይገባዋል” አሉ።

12ኤርምያስም፣ ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የሰማችሁትን ሁሉ በዚህ ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እንድናገር እግዚአብሔር ልኮኛል። 13አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። 14ስለ እኔ ከሆነ ግን እነሆ፤ በእጃችሁ ነኝ፤ መልካምና ተገቢ መስሎ የሚታያችሁን ሁሉ አድርጉብኝ። 15ነገር ግን የሰማችሁትን ይህን ሁሉ ቃል በጆሯችሁ እንድናገር እግዚአብሔር በርግጥ ስለ ላከኝ ብትገድሉኝ፣ የንጹሕ ሰው ደም በማፍሰሳችሁ እናንተ ራሳችሁንና ይህችን ከተማ፣ በውስጧም የሚኖረውን በደለኛ እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ።”

16ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሯልና ሊገደል አይገባውም” አሉ።

17ከአገሩ ሽማግሌዎችም አንዳንዶቹ ተነሥተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አሉ፤ 18“ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን፣ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ጽዮን እንደ ዕርሻ ትታረሳለች፤

ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤

የቤተ መቅደሱም ተራራ፣ ዳዋ የወረሰው ኰረብታ ይሆናል።’26፥18 ሚክ 3፥12

19“ታዲያ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም ሆነ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ገደሉትን? ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን ፈርቶ ምሕረት አልለመነምን? እግዚአብሔርስ በእነርሱ ላይ ለማምጣት ያሰበውን ቅጣት አልተወምን? በራሳችን ላይ እኮ ታላቅ ጥፋት እያመጣን ነው።”

20ደግሞም የቂርያትይዓሪም ሰው፣ የሸማያ ልጅ ኦርዮ፣ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ ሌላው ሰው ነበር፤ እርሱም እንደ ኤርምያስ በዚህች ከተማና በዚህ ምድር ላይ ትንቢት ተናግሮ ነበር። 21ንጉሥ ኢዮአቄም፣ የጦር አለቆቹና ባለሥልጣኖቹ ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኦርዮም ይህን ሰምቶ በፍርሀት ወደ ግብፅ ሸሸ። 22ይሁን እንጂ ንጉሥ ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንንና ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብፅ ላካቸው፤ 23እነርሱም ኦርዮን ከግብፅ አምጥተው፣ ወደ ንጉሥ ኢዮአቄም ወሰዱት፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው፤ ሬሳውንም ተራ ሰዎች በሚቀበሩበት ስፍራ ጣለው።

24ነገር ግን የሳፋን ልጅ አኪቃም ከኤርምያስ ጐን ስለ ቆመ፣ ኤርምያስ ይገደል ዘንድ ለሕዝቡ ዐልፎ አልተሰጠም።