ኤርምያስ 24 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 24:1-10

መልካሙና መጥፎው በለስ

1የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የኢዮአቄምን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንንና24፥1 በዕብራይስጡ ኢኮንያን፣ የኢዮአኪን አቻ ስም ነው። ባለሥልጣኖቹን እንዲሁም የይሁዳን ዐናጺዎችና ብረት ቀጥቃጮች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር ሁለት ቅርጫት በለስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ተቀምጦ አሳየኝ። 2አንዱ ቅርጫት፣ ቶሎ የደረሰ ፍሬ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረበት፣ በሌላው ቅርጫት ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ የማይቻል እጅግ መጥፎ በለስ ነበረበት።

3እግዚአብሔርም፣ “ኤርምያስ ሆይ፤ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ።

እኔም፣ “በለስን አያለሁ፤ ጥሩ የሆነው እጅግ መልካም ነው፤ የተበላሸው ግን እጅግ መጥፎ በመሆኑ ሊበላ የማይችል ነው” አልሁ።

4እንደ ገናም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 5“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ ከዚህ ስፍራ ወደ ባቢሎናውያን24፥5 ወይም ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳ ምርኮ በመልካም አስበዋለሁ። 6ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። 7እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

8“ ‘ነገር ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ እንደ ማይቻለው እንደ መጥፎ በለስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና ባለሥልጣኖቹን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የቀሩትንም ሆነ በግብፅ የሚኖሩትን፣ እንዲሁ አደርግባቸዋለሁ። 9በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉና የሚሰደቡ ይሆናሉ፤ በምበትናቸውም ስፍራ ሁሉ ለማላገጫና ለመተረቻ፣ ለመሣለቂያና ለርግማን አደርጋቸዋለሁ። 10ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ ሰይፍ፣ ራብና መቅሠፍት እሰድባቸዋለሁ።’ ”