ኤርምያስ 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 14:1-22

ድርቅ፣ ራብ፣ ሰይፍ

1ስለ ድርቅ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤

2“ይሁዳ ታለቅሳለች፤

ከተሞቿም ይማቅቃሉ፤

በምድር ላይ ተቀምጠው ይቈዝማሉ፤

ጩኸትም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ይሰማል።

3መሳፍንት አገልጋዮቻቸውን ውሃ ፍለጋ ይሰዳሉ፤

እነርሱ ወደ ውሃ ጕድጓዶች ይወርዳሉ፤

ነገር ግን ውሃ አያገኙም፤

ዐፍረውና ተስፋ ቈርጠው፣

ራሳቸውን ተከናንበው፣

ባዶ እንስራ ይዘው ይመለሳሉ።

4በምድሪቱ ዝናብ ስለሌለ፣

መሬቱ ተሰነጣጥቋል፤

ገበሬዎችም ዐፍረው፣

ራሳቸውን ተከናንበዋል።

5አንዳች ሣር ባለመኖሩ፣

የሜዳ አጋዘን እንኳ፣

እንደ ወለደች ግልገሏን ጥላ ትሄዳለች።

6የሜዳ አህዮች ባድማ ኰረብቶች ላይ ቆሙ፤

እንደ ቀበሮም አየር ፍለጋ አለከለኩ፤

ግጦሽ ባለመገኘቱ፣

ዐይኖቻቸው ፈዘዙ።”

7እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአንተ መኰብለል አብዝተናል፤

በአንተም ላይ ዐምፀናል፤

ኀጢአታችን ቢመሰክርብንም እንኳ፣

ስለ ስምህ ብለህ አንድ ነገር አድርግልን።

8አንተ የእስራኤል ተስፋ፤

በጭንቀት ጊዜ አዳኙ፣

ለምን በምድሪቱ እንደ ባዕድ፣

እንደ ሌት ዐዳሪ መንገደኛ ትሆናለህ?

9ግራ እንደ ተጋባ ሰው፣

ለመታደግም ኀይል እንዳጣ ተዋጊ ትሆናለህ?

እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በመካከላችን አለህ፤

በስምህም ተጠርተናል፤

እባክህ አትተወን።

10እግዚአብሔር ስለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፤

“መቅበዝበዝ እጅግ ይወድዳሉ፤

እግሮቻቸው አይገቱም፤

ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤

አሁን በደላቸውን ያስባል፤

በኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።”

11እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ለዚህ ሕዝብ በጎነት አትጸልይ፤ 12ቢጾሙም ጩኸታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ቢያቀርቡም አልቀበላቸውም፤ ነገር ግን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር አጠፋቸዋለሁ።”

13እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ! ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ዘለቄታ ያለው ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይላል ይሏቸዋል” አልሁ።

14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት14፥14 ወይም ራእይ፣ (ከንቱ) ሟርት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል። 15ስለዚህ በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሳልልካቸው፣ ‘ሰይፍና ራብ በዚች ምድር ላይ አይመጣም’ የሚሉ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ 16ትንቢቱ የተነገረለትም ሕዝብ ከሰይፍና ከራብ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይወድቃል፤ እነርሱንም ሆነ ሚስቶቻቸውን ወይም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቀብራቸው አይገኝም። ለበደላቸው የሚገባውንም ቅጣት በላያቸው አወርዳለሁ።

17“ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤

“ ‘ድንግሊቱ ልጄ፣ ሕዝቤ፣

በታላቅ ስብራት፣

በብርቱ ቍስል ተመትታለችና

ዐይኖቼ ቀንና ሌሊት፣ ሳያቋርጡ

እንባ ያፈስሳሉ

18ወደ ገጠር ብወጣ፣

በሰይፍ የተገደሉትን አያለሁ፤

ወደ ከተማ ብገባ፣ በራብ የወደቁትን አያለሁ

ነቢዩም ካህኑም፣

ወደማያውቁት አገር ሸሽተዋል።’ ”

19ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን?

ነፍስህስ ጽዮንን ተጸየፈቻትን?

ፈውስ እስከማይገኝልን ድረስ፣

ለምን ክፉኛ መታኸን?

ሰላምን ተስፋ አደረግን፤

ሆኖም በጎ ነገር አላገኘንም፤

የፈውስን ጊዜ ተጠባበቅን፤

ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነ።

20እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፋታችንን ዐውቀናልና፤

የአባቶቻችንን በደል ተረድተናልና፤

በርግጥም በአንተ ላይ ኀጢአት ሠርተናል።

21ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፤

የክብርህንም ዙፋን አታዋርድ።

ከእኛ ጋር የገባኸውን ኪዳን ዐስብ፤

አታፍርሰውም።

22ከአሕዛብ ከንቱ ጣዖቶች መካከል ዝናብ ሊያዘንብ የሚችል አለን?

ሰማያትስ በራሳቸው ማካፋት ይችላሉን?

አይ! አይችሉም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤

ይህን ሁሉ የምታደርግ አንተ ነህ፣

ስለዚህም ተስፋችን በአንተ ላይ ነው።