ኢዮብ 40 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዮብ 40:1-24

1እግዚአብሔርም ኢዮብን እንዲህ አለው፤

2“ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ተከራክሮ የሚረታው አለን?

እግዚአብሔርን የሚወቅሥ እርሱ መልስ ይስጥ!”

3ኢዮብም ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፤

4“እኔ ከንቱ ሰው፣ ምን እመልስልሃለሁ?

እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።

5አንድ ጊዜ ተናገርሁ፤ የምመልሰው የለኝም፤

ሁለተኛም ተናገርሁ፤ ከእንግዲህ አንዳች አልጨምርም።”

6እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ፣ ለኢዮብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤

7“እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤

እኔ እጠይቅሃለሁ፤

አንተም መልስልኝ።

8“ፍርዴን ታቃልላለህን?

ወይስ አንተ ጻድቅ ለመሆን እኔን ትኰንናለህ?

9እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን?

ድምፅህስ እንደ እርሱ ድምፅ ሊያንጐደጕድ ይችላልን?

10እንግዲያስ ክብርንና ልዕልናን ተጐናጸፍ፤

ግርማ ሞገስንም ተላበስ፤

11ቍጣህን አፍስስ፤

ትዕቢተኛውን ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው፤

12ትዕቢተኛውን ሰው ሁሉ ተመልክተህ ዝቅ አድርገው፤

ክፉዎችንም በቆሙበት ስፍራ አድቅቃቸው።

13ሁሉንም በአንድ ላይ ከዐፈር ደባልቃቸው፤

ፊታቸውንም በመቃብር ውስጥ ሸፍን።

14እኔም ቀኝ እጅህ እንደምታድንህ፣

በዚያን ጊዜ አረጋግጬ እቀበላለሁ።

15“አንተን እንደ ፈጠርሁ፣ የፈጠርሁትን

‘ብሄሞት’40፥15 ጕማሬ ወይም ዝሆን ተመልከት፤

እንደ በሬ ሣር ይበላል፤

16ብርታቱ ወገቡ ውስጥ፣

ኀይሉም በሆዱ ጡንቻ ላይ ነው።

17ጅራቱ40፥17 ምናልባት ግንዱ ማለት ሊሆን ይችላል። እንደ ጥድ ዛፍ ይወዛወዛል፤

የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።

18ዐጥንቱ እንደ ናስ ቱቦ፣

እጅና እግሮቹም እንደ ብረት ዘንግ ናቸው።

19እርሱ የእግዚአብሔር ሥራ አውራ ነው፤

በሰይፍ ሊቀርበውም የሚችል ፈጣሪው ብቻ ነው።

20ኰረብቶች ምግቡን ያበቅሉለታል፤

አውሬዎችም ሁሉ በዙሪያው ይፈነጫሉ።

21በውሃ ላይ በሚያድጉ ዕፀዋት ጥላ ሥር ይተኛል፤

በረግረግ ስፍራ ደንገል መካከል ይደበቃል።

22በውሃ ላይ የሚያድጉ ዕፀዋት በጥላቸው ይጋርዱታል፤

የወንዝ አኻያ ዛፎች ይሸፍኑታል።

23ወንዙ በኀይል ቢጐርፍም፣ አይደነግጥም፤

ዮርዳኖስ እስከ አፉ ቢሞላም፣ እርሱ ተረጋግቶ ይቀመጣል።

24ዐይኑን ሸፍነህ ልትይዘው፣

አጥምደህም አፍንጫውን ልትበሳ ትችላለህ?