ኢዮብ 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዮብ 3:1-26

ኢዮብ ይናገራል

1ከዚህ በኋላ፣ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ፤ 2እንዲህም አለ፤

3“የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፤

‘ወንድ ልጅ ተፀነሰ’ የተባለበት ሌሊት።

4ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤

እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፤

ብርሃንም አይብራበት።

5ጨለማና የሞት ጥላ3፥5 ወይም ከባድ ጥላ ይውረሱት፤

ደመናም በላዩ ላይ ይረፍ፤

ብርሃኑን ጽልመት ይዋጠው።

6ያ ሌሊት በድቅድቅ ጨለማ ይያዝ፤

ከዓመቱ ቀናት ጋር አይቈጠር፤

ከወራቱ በአንዱም ውስጥ አይግባ።

7ያ ሌሊት መካን ይሁን፤

እልልታም አይሰማበት።

8ሌዋታንን ለማነሣሣት የተዘጋጁ፤

ቀንንም3፥8 ወይም ባሕርን የሚረግሙ ያን ቀን ይርገሙት።

9አጥቢያ ኮከቦቹ ይጨልሙ፤

ብርሃንን እየጠበቀ ይጣ፤

የንጋት ጮራ ሲፈነጥቅ አይይ።

10መከራን ከዐይኔ ይሰውር ዘንድ፣

የእናቴን ማሕፀን ደጅ በላዬ አልዘጋምና።

11“ምነው ገና ስወለድ በጠፋሁ!

ምነው ከማሕፀን ስወጣ በሞትሁ!

12የሚቀበሉኝ ጕልበቶች፤

የሚያጠቡኝ ጡቶች ለምን ተገኙ?

13ይህን ጊዜ በሰላም በተኛሁ፣

አንቀላፍቼም ባረፍሁ ነበር፤

14አሁን ፈርሶ የሚታየውን ስፍራ ለራሳቸው ካሠሩት፣

ከምድር ነገሥታትና ከአማካሪዎች ጋር፣

15ቤታቸውን በብር ከሞሉ፣

ወርቅም ከነበራቸው ገዦች ጋር ባረፍሁ ነበር።

16ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፣

ብርሃንም እንዳላየ ሕፃን በሆንሁ ነበር።

17በዚያ ክፉዎች ማወካቸውን ይተዋሉ፤

ደካሞችም በዚያ ያርፋሉ፤

18ምርኮኞች እንደ ልባቸው ይቀመጣሉ፤

ከእንግዲህም የአስጨናቂዎቻቸውን ጩኸት አይሰሙም።

19ትንሹም ትልቁም በዚያ ይገኛል፤

ባሪያው ከጌታው ነጻ ወጥቷል።

20“በመከራ ላሉት ብርሃን፣

ነፍሳቸው ለተማረረች ሕይወት ለምን ተሰጠ?

21ሞትን በጕጕት ለሚጠብቁና ለማያገኙት፣

ከተሰወረ ሀብት ይልቅ ለሚሹት፣

22ወደ መቃብር ሲቃረቡ ደስ እያላቸው፣

በሐሤት ለሚሞሉ ሕይወት ለምን ተሰጠ?

23መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፤

እግዚአብሔርም በዐጥር ላጠረው፣

ሕይወት ለምን ተሰጠ?

24ትካዜ ምግብ ሆኖኛልና፤

የሥቃይ ጩኸቴም እንደ ውሃ ይፈስሳል።

25የፈራሁት ነገር መጥቶብኛል፤

የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።

26ሰላም የለኝም፤ ርጋታም የለኝም፤

ሁከት እንጂ ዕረፍት የለኝም።”