ኢዮብ 24 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዮብ 24:1-25

1“ሁሉን የሚችል አምላክ ለምን የፍርድ ቀን አይወስንም?

እርሱን የሚያውቁትስ ለምን ያን ቀን እንዲያው ይጠባበቃሉ?

2ሰዎች ድንበር ይገፋሉ፤

የሰረቁትን መንጋ ያሰማራሉ።

3የድኻ ዐደጉን አህያ ቀምተው ይሄዳሉ፤

የመበለቲቱንም በሬ በመያዣነት ይወስዳሉ።

4ችግረኛውን ከመንገድ ያስወግዳሉ፤

የምድሪቱም ድኾች ይሸሸጋሉ።

5በምድረ በዳ እንዳሉ የሜዳ አህዮች፣

ድኾች ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ፤

ከበረሓው ምድር ለልጆቻቸው ምግብ ይሻሉ።

6ከሜዳ መኖ ይሰበስባሉ፤

ከክፉዎች የወይን ቦታም ይቃርማሉ።

7ዕራቍታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፤

በብርድም ጊዜ የሚለብሱት የላቸውም።

8ከተራራ በሚወርድ ዝናብ በስብሰዋል፤

መጠለያ ዐጥተው ቋጥኝ ዐቅፈዋል።

9አባት የሌለው ልጅ ከዕቅፍ ተነጥቋል፤

የድኻውም ልጅ በዕዳ ተይዟል።

10ዕራቍታቸውን ያለ ልብስ ይሄዳሉ፤

ነዶ ይሸከማሉ፤ ግን ይራባሉ።

11በየተረተሩ24፥11 ወይም ከወፍጮዎች መካከል የወይራ ዘይት ማለት ነው፤ ሆኖም የዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። የወይራ ዘይት ያወጣሉ፤

ወይን እየጠመቁ፣ ራሳቸው ግን ይጠማሉ፤

12የሟቾች ጣር ጩኸት ከከተማዋ ይሰማል፤

የቈሰሉት ሰዎች ነፍስ ለርዳታ ይጮኻል፤

እግዚአብሔር ግን ተጠያቂዎቹን ዝም ብሏል።

13“በብርሃን ላይ የሚያምፁ፣

ጐዳናውን የማያውቁ፣

በመንገዱም የማይጸኑ አሉ።

14ቀኑ ሲመሽ፣ ነፍሰ ገዳይ ይነሣል፤

ድኾችንና ችግረኞችን ይገድላል፤

በሌሊትም እንደ ሌባ ያደባል፤

15አመንዝራ በዐይኑ ድንግዝግዝታን ይጠባበቃል፤

‘ማንም አያየኝም’ ብሎ ያስባል፤

ፊቱንም ይሸፍናል።

16በጨለማ፣ ቤት ሰርስረው ይገባሉ፤

በቀን ግን ይሸሸጋሉ፤

ብርሃንንም አይፈልጉም።

17ድቅድቅ ጨለማ ለሁላቸው እንደ ንጋት24፥17 ወይም ለእነርሱ ንጋት እንደ ሞት ጥላ ነው ነው፤

አሸባሪውን ጨለማ24፥17 ወይም ከሞት ጥላ ማለት ነው። ይወዳጃሉ።

18“ይሁን እንጂ፣ በውሃ ላይ የሚኵረፈረፍ ዐረፋ ናቸው፤

የወይን ቦታው ሰው የማይደርስበት፣

ርስታቸው ርጉም ነው።

19ድርቅና ሙቀት የቀለጠውን በረዶ ከቦታው እንደሚያስወግድ፣

ሲኦልም24፥19 አንዳንድ ቅጆች፣ መቃብር ይሉታል ኀጢአተኞችን ትነጥቃለች።

20የተሸከመቻቸው ማሕፀን ትረሳቸዋለች፤

ትል ይቦጠቡጣቸዋል፤

ክፉዎች እንደ ዛፍ ይሰበራሉ፤

የሚያስታውሳቸውም የለም።

21የማትወልደውን መካኒቱን ይቦጠቡጣሉ፤

ለመበለቲቱም አይራሩም።

22ነገር ግን እግዚአብሔር ብርቱዎችን በኀይሉ ጐትቶ ይጥላል፤

ቢደላደሉም የሕይወት ዋስትና የላቸውም።

23ያለ ሥጋት እንዲኖሩ ትቷቸው ይሆናል፤

ዐይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው።

24ለጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሆኖም ይጠፋሉ፤

ዝቅ ዝቅ ብለው፤ እንደ ሌሎቹ ይከማቻሉ።

እንደ እህል ራስም ይታጨዳሉ።

25“ይህ እንዲህ ካልሆነማ፣ የሚያስተባብለኝ ማን ነው?

ቃሌን ከንቱ የሚያደርገውስ ማን ነው?”