ኢያሱ 24 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢያሱ 24:1-33

ቃል ኪዳኑ በሴኬም ታደሰ

1ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ።

2ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ24፥2 በዚህ እንዲሁም ቍጥር 3፡14 እና 15 ላይ የተጠቀሰው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው።፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። 3እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት። 4ለይስሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብፅ ወረዱ።

5“ ‘ከዚያም ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ባመጣሁት መቅሠፍት ግብፃውያንን አስጨንቄ፣ እናንተን ከዚያ አወጣኋችሁ። 6አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ መጣችሁ፤ ግብፃውያንም በሠረገሎችና24፥6 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይቻላል። በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር24፥6 ዕብራይስጡ ያም ሳውፍ ይላል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው። ድረስ ተከታተሏቸው። 7እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብፃውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ።

8“ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ። 9የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤ 10እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ።

11“ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ነዋሪዎች ወጓችሁ። 12በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። 13ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’

14“አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብፅ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። 15እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”

16ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ። 17እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብፅ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጕዟችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው። 18እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።”

19ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ እርሱ ቅዱስ አምላክና፤ ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ዐመፃችሁን ወይም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። 20እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።”

21ሕዝቡ ግን ኢያሱን፣ “የለም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት።

22ከዚያም ኢያሱ፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ መርጣችኋልና በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው።

እነርሱም፣ “አዎን ምስክሮች ነን” ሲሉ መለሱ።

23ኢያሱም፣ “እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር መልሱ” አላቸው።

24ሕዝቡም ኢያሱን፣ “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እንታዘዝለታለንም” አሉት።

25በዚያን ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የሚመሩበትንም ደንብና ሥርዐት እዚያው ሴኬም ሰጣቸው። 26ኢያሱም እነዚህን ቃሎች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ በባሉጥ ዛፍ ሥር፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ስፍራ አጠገብ አቆመው።

27ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፣ “እነሆ፤ ይህ ድንጋይ፣ እግዚአብሔር የተናገረንን ሁሉ ሰምቷል፣ በእኛም ይመሰክርብናል፤ እናንተም በአምላካችሁ ዘንድ እውነተኞች ሆናችሁ ባትገኙ ምስክር ይሆንባችኋል” አላቸው።

ኢያሱ በተሰፋዪቱ ምድር ተቀበረ

24፥29-31 ተጓ ምብ – መሳ 2፥6-9

28ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ ወደየርስቱ እንዲሄድ አሰናበተ።

29ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። 30በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው፣ ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት በተምናሴራ ቀበሩት።

31ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በሕይወት በኖሩትና እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አመለኩ።

32እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጡት የዮሴፍ ዐፅም፣ ያዕቆብ ከሰኬም አባት ከኤሞር በመቶ ሰቅል24፥32 ዕብራይስጡ አንድ መቶ ከሲታሃስ ይላል፤ ክብደቱና ዋጋው በትክክል የማይታወቅ የገንዘብ ዐይነት ነው። ብር በገዛው በሴኬም ምድር ተቀበረ፤ ይህችም የዮሴፍ ዘሮች ርስት ሆነች።

33እንዲሁም የአሮን ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በሚገኘው ለልጁ ለፊንሐስ በዕጣ በደረሰው በጊብዓ ምድር ተቀበረ።