ሮሜ 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሮሜ 11:1-36

የእስራኤል ቅሬታዎች

1እንግዲህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተዋቸውን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! እኔ ራሴ ከብንያም ነገድ፣ የአብርሃም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ። 2እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም። ኤልያስ በእስራኤል ላይ ክስ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንዳቀረበ፣ መጽሐፍ ስለ እርሱ ምን እንደሚል አታውቁምን? 3“ጌታ ሆይ፤ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ሊገድሉኝም ይፈልጋሉ።” 4እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ግን ምን ነበር? “ለበኣል ያልሰገዱትን ሰባት ሺሕ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ።”

5በአሁኑ ጊዜም እንደዚሁ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ። 6እንግዲህ በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም፤ በሥራ ቢሆንማ ኖሮ ጸጋ፣ ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር።11፥6 አንዳንድ ቅጆች በሥራ ቢሆንማ ኖሮ ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር፤ በጸጋ ከሆነም ሥራ፣ ሥራ መሆኑ ይቀራል ይላሉ።

7እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ልባቸው ደነደነ፤ 8እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤

“ዐይናቸው እንዳያይ፣

ጆሯቸውም እንዳይሰማ፣

እግዚአብሔር እስከዚህ ቀን ድረስ፣

የድንዛዜ መንፈስ ሰጣቸው።”

9ዳዊትም አለ፤

“ማእዳቸው አሽክላና ወጥመድ፣

ዕንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው።

10ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጋረዱ፤

ወገባቸውም ለዘላለም ይጕበጥ።”

የተዳቀሉ ቅርንጫፎች

11ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይደለም፤ ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቷል። 12ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸው ምን ያህል ታላቅ በረከት ያመጣ ይሆን?

13አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤ 14ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው። 15የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? 16በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።

17ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘውን በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣ 18በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኵራራ። ብትኰራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ ግን አንተን ይሸከምሃል እንጂ። 19እንግዲህ፣ “ቅርንጫፎች የተሰበሩት እኔ እንድገባ ነው” ትል ይሆናል። 20ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን። 21እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው፣ ለአንተም አይራራልህምና።

22እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭካኔ ተመልከት፤ ጭካኔውም በወደቁት ላይ ነው፤ ቸርነቱ ግን በቸርነቱ ውስጥ እስካለህ ድረስ ለአንተ ነው፤ አለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ። 23እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ፣ ተመልሰው ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያስገባቸው ይችላልና። 24የበረሓ ከሆነው የወይራ ዛፍ የተቈረጥህና ተፈጥሮህ ወዳልሆነው ወደ መልካሙ ወይራ የገባህ ከሆንህ፣ በተፈጥሯቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት እነዚህ ወደ ራሳቸው ወይራ ዛፍ መግባታቸውማ ምን ያህል ይሆን?

እስራኤል ሁሉ ይድናል

25ወንድሞች ሆይ፤ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ፣ ይህን ምስጢር ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል በድንዳኔ ውስጥ ዐልፋለች። 26ስለዚህ እስራኤል ሁሉ ይድናሉ፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤

“አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤

ከያዕቆብም ክፋትን ያስወግዳል።

27ኀጢአታቸውንም ሳስወግድ፣

ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳኔ ይህ ነው።”11፥27 ወይም ይህ ይሆናል

28እንደ ምሥራቹ ቃል ለእናንተ ሲባል ጠላቶች ናቸው፤ እንደ ምርጫ ከሆነ ግን፣ ለአባቶች ሲባል የተወደዱ ናቸው፤ 29የእግዚአብሔር ስጦታና ጥሪ ጸጸት የለበትም። 30እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ እንደ ነበራችሁ፣ ከእነርሱ አለመታዘዝ የተነሣ አሁን ምሕረት እንዳገኛችሁ ሁሉ፣ 31እግዚአብሔር ለእናንተ ምሕረት ከማድረጉ የተነሣ፣ እነርሱም ምሕረት ያገኙ ዘንድ አሁን11፥31 አንዳድ ቅጆች አሁን የሚለው ቃል የላቸውም። የማይታዘዙ ልጆች ሆነዋል፤ 32እግዚአብሔር ለሁሉም ምሕረት ያደርግ ዘንድ ሰውን ሁሉ ባለመታዘዝ ዘግቶታልና።

ውዳሴ

33የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት11፥33 ወይም ባለጠግነቱ፣ ጥበቡና ዕውቀቱ እንዴት ጥልቅ ነው!

ፍርዱ አይመረመርም፤

ለመንገዱም ፈለግ የለውም!

34“የጌታን ልብ ያወቀ ማነው?

አማካሪውስ የነበረ ማን ነው?”

35“እግዚአብሔር መልሶ እንዲሰጠው፣

ለእግዚአብሔር ያበደረ ከቶ ማን ነው?”

36ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤

ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።