ራእይ 20 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ራእይ 20:1-15

የሺሕ ዓመቱ መንግሥት

1የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። 2እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺሕ ዓመት አሰረው። 3ሺሑ ዓመት እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በእርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።

4ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ ደግሞም ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል የተሰየፉትን ሰዎች ነፍሶች አየሁ። እነርሱ ለአውሬው ወይም ለእርሱ ምስል አልሰገዱም፤ በግንባራቸው ወይም በእጃቸው ላይ የአውሬውን ምልክት አልተቀበሉም፤ እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺሕ ዓመት ነገሡ። 5የቀሩት ሙታን ግን ሺሑ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። 6በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ሺሕ ዓመት ይነግሣሉ።

የሰይጣን የመጨረሻ ዕጣ

7ሺሑም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ 8በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፣ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል። ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው። 9እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው። 10ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።

ሙታን ተፈረደባቸው

11ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው። 13ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት። 14ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። 15ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ።