ምሳሌ 29 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 29:1-27

1ከብዙ ተግሣጽ በኋላ ዐንገቱን የሚያደነድን ሰው፣

በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።

2ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤

ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል።

3ጥበብን የሚወድድ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤

የአመንዝራዎች ወዳጅ ግን ሀብቱን ያባክናል።

4ፍትሕን በማስፈን ንጉሥ አገርን ያረጋጋል፤

ጕቦ ለማግኘት የሚጐመጅ ግን ያፈራርሳታል።

5ባልንጀራውን የሚሸነግል፣

ለገዛ እግሩ መረብ ይዘረጋል።

6ክፉ ሰው በራሱ ኀጢአት ይጠመዳል፤

ጻድቅ ግን ይዘምራል፤ ደስም ይለዋል።

7ጻድቅ ለድኾች ፍትሕ ይጨነቃል፤

ክፉ ሰው ግን ደንታ የለውም።

8ተሳዳቢዎች ከተማን ያውካሉ፤

ጠቢባን ግን ቍጣን ያበርዳሉ።

9ጠቢብ ሰው ከተላላ ጋር ወደ ሸንጎ ቢሄድ፣

ተላላ ይቈጣል፤ ያፌዛል፤ ሰላምም አይኖርም።

10ደም የተጠሙ ሰዎች ሐቀኛን ሰው ይጠላሉ፤

ቅን የሆነውንም ለመግደል ይሻሉ።

11ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቅቀዋል፤

ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል።

12ገዥ የሐሰት ወሬ የሚሰማ ከሆነ፣

ሹማምቱ ሁሉ ክፉዎች ይሆናሉ።

13ድኻውና ጨቋኙ የጋራ ነገር አላቸው፤

እግዚአብሔር ለሁለቱም የዐይን ብርሃንን ሰጥቷቸዋል።

14ንጉሥ ለድኻ ትክክለኛ ፍርድ ቢሰጥ፣

ዙፋኑ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

15የተግሣጽ በትር ጥበብን ታጐናጽፋለች፤

መረን የተለቀቀ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል።

16ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ኀጢአት ይበዛል፤

ጻድቃን ግን የእነርሱን ውድቀት ያያሉ።

17ልጅህን ቅጣው፤ ሰላም ይሰጥሃል፤

ነፍስህንም ደስ ያሰኛታል።

18ራእይ በሌለበት ሕዝብ መረን ይሆናል፤

ሕግን የሚጠብቅ ግን የተባረከ ነው።

19አገልጋይ በቃል ብቻ ሊታረም አይችልም፤

ቢያስተውለውም እንኳ በጀ አይልም።

20በችኰላ የሚናገርን ሰው ታያለህን?

ከእርሱ ይልቅ ተላላ ተስፋ አለው።

21ሰው አገልጋዩን ከልጅነቱ ጀምሮ ቢያቀማጥል፣

የኋላ ኋላ ሐዘን29፥21 በዕብራይስጡ የዚህ ቃል ትርጓሜ በርግጠኝነት አይታወቅም። ያገኘዋል።

22ቍጡ ሰው ጠብን ይጭራል፤

ግልፍተኛም ብዙ ኀጢአት ይሠራል።

23ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤

ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብርን ይጐናጸፋል።

24የሌባ ግብረ አበር የገዛ ራሱ ጠላት ነው፤

የመሐላውን ርግማን እየሰማ ጭጭ ይላል።

25ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤

በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል።

26ብዙዎች በገዥ ፊት ተደማጭነት ማግኘት ይሻሉ፤

ሰው ፍትሕ የሚያገኘው ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

27ጻድቃን አታላዮችን ይጸየፋሉ፤

ክፉዎችም ቅኖችን ይጠላሉ።