ምሳሌ 28 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 28:1-28

1ክፉ ሰው ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤

ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ልበ ሙሉ ነው።

2አገር ስታምፅ፣ ገዦቿ ይበዛሉ፤

አስተዋይና ዐዋቂ ሰው ግን ሥርዐትን ያሰፍናል።

3ድኾችን የሚያስጨንቅ ሰው፣28፥3 ወይም ድኻ

ሰብል እንደሚያጠፋ ኀይለኛ ዝናብ ነው።

4ሕግን የሚተዉ ክፉዎችን ያወድሳሉ፤

ሕግን የሚጠብቁ ግን ይቋቋሟቸዋል።

5ክፉዎች ፍትሕን አያስተውሉም፤

እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሙሉ በሙሉ ያውቁታል።

6በአካሄዱ ነውር የሌለበት ድኻ፣

መንገዱ ጠማማ ከሆነ ባለጠጋ ይሻላል።

7ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤

ከሆዳሞች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን አባቱን ያዋርዳል።

8በከፍተኛ ወለድ ሀብቱን የሚያካብት፣

ለድኻ ለሚራራ፣ ለሌላው ሰው ያከማችለታል።

9ሕግን ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣

ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው።

10ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚመራ፣

በቈፈረው ጕድጓድ ይገባል፤

ንጹሓን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ።

11ባለጠጋ ራሱን ጠቢብ አድርጎ ይቈጥር ይሆናል፤

አስተዋይ የሆነ ድኻ ግን መርምሮ ያውቀዋል።

12ጻድቃን ድል ሲነሡ ታላቅ ደስታ ይሆናል፤

ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ግን ሕዝብ ይሸሸጋል።

13ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤

የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል።

14እግዚአብሔርን ዘወትር የሚፈራ ሰው ቡሩክ ነው፤

ልቡን የሚያደነድን ግን መከራ ላይ ይወድቃል።

15ታዳጊ በሌለው ሕዝብ ላይ የተሾመ ጨካኝ ገዥ፣

እንደሚያገሣ አንበሳ ወይም ተንደርድሮ እንደሚይዝ ድብ ነው።

16ጨካኝ ገዥ ማመዛዘን ይጐድለዋል፤

አለአግባብ የሚገኝን ጥቅም የሚጸየፍ ግን ዕድሜው ይረዝማል።

17የሰው ደም ያለበት ሰው፣

ዕድሜ ልኩን ሲቅበዘበዝ ይኖራል፤

ማንም ሰው አይርዳው።

18አካሄዱ ነቀፋ የሌለበት ሰው ክፉ አያገኘውም፤

መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ድንገት ይወድቃል።

19መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤

ከንቱ ተስፋን ይዞ የሚጓዝ ግን ድኽነትን ይወርሳል።

20ታማኝ ሰው እጅግ ይባረካል፤

ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ ግን ከቅጣት አያመልጥም።

21አድልዎ ማድረግ መልካም አይደለም፤

ሰው ግን ለቍራሽ እንጀራ ሲል በደል ይፈጽማል።

22ስስታም ሀብት ለማከማቸት ይስገበገባል፤

ድኽነት እንደሚጠብቀውም አያውቅም።

23ሸንጋይ አንደበት ካለው ይልቅ፣

ሰውን የሚገሥጽ ውሎ ዐድሮ ይወደዳል።

24ከአባት ከእናቱ ሰርቆ፣

“ይህ ጥፋት አይደለም” የሚል የአጥፊ ተባባሪ ነው።

25ሥሥታም ሰው ጠብን ያነሣሣል፤

በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይባረካል።

26በራሱ የሚታመን ተላላ ነው፤

በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም።

27ለድኾች የሚሰጥ አይቸገርም፤

አይቷቸው እንዳላየ የሚሆን ግን ብዙ ርግማን ይደርስበታል።

28ክፉዎች ሥልጣን በሚይዙ ጊዜ ሕዝብ ይሸሸጋል፤

ክፉዎች በሚጠፉበት ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።