ምሳሌ 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 14:1-35

1ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤

ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች።

2አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤

መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል።

3የተላላ ሰው ንግግር ለጀርባው በትር ታስከትልበታለች፤

የጥበበኛ ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች።

4በሬዎች በሌሉበት ገንዳው ባዶ ይሆናል፤

በበሬ ጕልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል።

5ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤

ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይዘከዝካል።

6ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤

ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች።

7ከተላላ ሰው ራቅ፣

ከከንፈሮቹ ዕውቀት አታገኝምና።

8የአስተዋዮች ጥበብ መንገዳቸውን ልብ ማለት ነው፤

የተላሎች ሞኝነት ግን መታለል ነው።

9ተላሎች በሚያቀርቡት የበደል ካሳ ያፌዛሉ፤

በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ ትገኛለች።

10እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤

ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም።

11የክፉዎች ቤት ይፈርሳል፤

የቅኖች ድንኳን ግን ይስፋፋል።

12ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤

በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል።

13በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል፤

ደስታም በሐዘን ሊፈጸም ይችላል።

14ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱ የእጃቸውን ሙሉ ዋጋ ይቀበላሉ፤

ደግ ሰውም ወሮታውን ያገኛል።

15ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤

አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።

16ጠቢብ ሰው ጥንቁቅ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤

ተላላ ግን ችኵልና ደንታ ቢስ ነው።

17ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል፤

መሠሪም ሰው አይወደድም።

18ብስለት የሌላቸው ተላላነትን ይወርሳሉ፤

አስተዋዮች ግን ዕውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።

19ክፉዎች በደጎች ፊት፣

ኀጥኣንም በጻድቃን ደጅ ያጐነብሳሉ።

20ድኾችን ወዳጆቻቸው እንኳ ይጠሏቸዋል፤

ባለጠጎች ግን ብዙ ወዳጆች አሏቸው።

21ጎረቤቱን የሚንቅ ኀጢአት ይሠራል፤

ለተቸገሩት የሚራራ ግን ቡሩክ ነው።

22ክፉ ነገር የሚያቅዱ ከትክክለኛው መንገድ ይወጡ የለምን?

በጎ ነገር የሚያቅዱ ግን ፍቅርንና ታማኝነትን ያተርፋሉ።14፥22 ወይም ታማኝነትን ያሳያሉ

23ለፍተው የሠሩት ሁሉ ትርፍ ያስገኛል፤

ከንቱ ወሬ ግን ወደ ድኽነት ያመራል።

24ጠቢባን ብልጽግና ዘውዳቸው ነው፤

የተላሎች ተላላነት ግን ፍሬው ከንቱነት ነው።

25እውነተኛ ምስክር ሕይወት ያድናል፤

ሐሰተኛ ምስክር ግን አባይ ነው።

26እግዚአብሔርን የሚፈራ ጽኑ ዐምባ አለው፤

ልጆቹም መጠጊያ ይኖራቸዋል።

27እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤

ሰውን ከሞት ወጥመድ ያድነዋል።

28የሕዝብ ብዛት የንጉሥ ክብር ሲሆን፣

የዜጎች ማነስ ግን ለገዥ መጥፊያው ነው።

29ታጋሽ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤

ግልፍተኛ ሰው ግን ቂልነትን ይገልጣል።

30ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል፤

ቅናት ግን ዐጥንትን ያነቅዛል።

31ድኾችን የሚያስጨንቅ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤

ለተቸገሩ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል።

32ክፉዎች በክፋታቸው ይወድቃሉ፤

ጻድቃን ግን በሞት ጊዜ እንኳ መጠጊያ አላቸው።

33ጥበብ በአስተዋዮች ልብ ታድራለች፤

በተላሎች መካከል ራሷን ትገልጣለች።14፥33 ዕብራይስጡ፣ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርሰት ትርጕሞች በተላሎች ልብ ግን አትታወቅም ይላሉ።

34ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤

ኀጢአት ግን ለየትኛውም ሕዝብ ውርደት ነው።

35ጠቢብ አገልጋይ ንጉሥን ደስ ያሰኛል፤

አሳፋሪ አገልጋይ ግን ቍጣውን በራሱ ላይ ያመጣል።