መዝሙር 94 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 94:1-23

መዝሙር 94

የእግዚአብሔር ፍትሕ

1የበቀል አምላክ፣ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤

የበቀል አምላክ ሆይ፤ ደምቀህ ተገለጥ።

2አንተ የምድር ዳኛ ሆይ፤ ተነሥ፤

ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው።

3ክፉዎች እስከ መቼ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ?

4የእብሪት ቃላት ያዥጐደጕዳሉ፤

ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጕራ ይነዛሉ።

5እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤

ርስትህንም አስጨነቁ።

6መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤

የድኻ ዐደጉንም ነፍስ አጠፉ።

7እነርሱም “እግዚአብሔር አያይም፤

የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ።

8እናንት በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤

እናንት ቂሎች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?

9ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?

10ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣

ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?

11እግዚአብሔር የሰው ሐሳብ መና፣

ከንቱም እንደ ሆነ ያውቃል።

12እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣

ከሕግህም የምታስተምረው ሰው ምስጉን ነው።

13ለኀጢአተኞች ጕድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣

እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ።

14እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤

ርስቱንም አይተውም።

15ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤

ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል።

16ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው?

ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር የሚሟገትልኝ ማን ነው?

17እግዚአብሔር ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣

ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር።

18እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣

እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ።

19የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣

ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።

20ዐመፃን ሕጋዊ የሚያደርግ፣

የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር ሊያብር ይችላልን?

21በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤

በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ።

22ለእኔ ግን እግዚአብሔር ምሽግ፣

አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል።

23በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤

በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤

እግዚአብሔር አምላካችን ይደመስሳቸዋል።