መዝሙር 84 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 84:1-12

መዝሙር 84

ወደ መቅደሱ ጕዞ መዝሙር

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት የሚዜም የቆሬ ልጆች መዝሙር።

1የሰራዊት አምላክ ሆይ፤

ማደሪያህ ምንኛ የተወደደ ነው!

2ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፤

እጅግም ትጓጓለታለች፤

ልቤና ሥጋዬም፣

ለሕያው አምላክ እልል በሉ።

3ንጉሤና አምላኬ የሰራዊት አምላክ ሆይ፤

መሠዊያህ ባለበት ስፍራ፣

ድንቢጥ እንኳ መኖሪያ ቤት፣

ዋኖስም ጫጩቶቿን የምታኖርበት ጐጆ አገኘች።

4በቤትህ የሚኖሩ የተባረኩ ናቸው፤

እነርሱም ለዘላለም ያመሰግኑሃል። ሴላ

5አንተን ብርታታቸው ያደረጉ፣

በልባቸው የጽዮንን መንገድ የሚያስቡ ቡሩካን ናቸው።

6በልቅሶ ሸለቆ በሚያልፉበት ጊዜ፣

የምንጭ መፍለቂያ ቦታ ያደርጉታል፤

የበልጕም ዝናብ ያረሰርሰዋል።84፥6 ወይም ይባርከዋል

7ከኀይል ወደ ኀይል ይሸጋገራሉ፤

እያንዳንዱም በጽዮን ባለው አምላክ ፊት ይቀርባል።

8የሰራዊት አምላክ ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤

የያዕቆብ አምላክ ሆይ አድምጠኝ። ሴላ

9አምላክ ሆይ፤ ጋሻችንን84፥9 ወይም ልዑል እይልን፤

የቀባኸውንም ተመልከት።

10በሌላ ስፍራ ሺሕ ቀን ከመኖር፣

በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል፤

በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፣

በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ።

11እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤

እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤

እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።

12የሰራዊት አምላክ ሆይ፤

በአንተ የታመነ ሰው ቡሩክ ነው።