መዝሙር 73 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 73:1-28

ሦስተኛ መጽሐፍ

ከመዝሙር 73–89

መዝሙር 73

የፍትሕ አሸናፊነት

የአሳፍ መዝሙር።

1እግዚአብሔር ልባቸው ንጹሕ ለሆነ፣

ለእስራኤል እንዴት ቸር ነው!

2እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣

አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ።

3ክፉዎች ሲሳካላቸው አይቼ፣

በዐመፀኞች ቀንቼ ነበርና።

4አንዳች ጣር የለባቸውም፤

ሰውነታቸውም ጤናማና የተደላደለ ነው።

5በሰዎች የሚደርሰው ጣጣ አይደርስባቸውም፤

እንደ ማንኛውም ሰው መከራ አያገኛቸውም።

6ስለዚህ ትዕቢት የዐንገት ጌጣቸው ነው፤

ዐመፅንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈዋል።

7የሠባ ዐይናቸው ይጕረጠረጣል፤73፥7 የዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሱርስቱና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ ከደነደነው ልባቸው በደል ይወጣል ይላል።

ልባቸውም በከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይፈስሳል።

8በፌዝና በክፋት ይናገራሉ፤

ቀና ቀና ብለውም በዐመፅ ይዝታሉ።

9አፋቸውን በሰማይ ላይ ያላቅቃሉ፤

አንደበታቸውም ምድርን ያካልላል።

10ስለዚህ ሕዝቡ ወደ እነርሱ ይነጕዳል፤

ውሃቸውንም በገፍ73፥10 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ይጠጣሉ።

11“ለመሆኑ እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል?

በልዑልስ ዘንድ ዕውቀት አለ?” ይላሉ።

12እንግዲህ፣ ክፉዎች ይህን ይመስላሉ፤

ሁልጊዜ ግድ የለሽና ሀብት በሀብት ናቸው።

13ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤

እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሯል!

14ቀኑን ሙሉ ተቀሠፍሁ፤

ጧት ጧትም ተቀጣሁ።

15“እኔ እንደዚህ እናገራለሁ” ብልማ ኖሮ፣

የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር።

16ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣

አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ።

17ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣

መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር።

18በርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥሃቸው፤

ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው።

19እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ!

በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ።

20ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣

ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣

እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ።

21ነፍሴ በተማረረች ጊዜ፣

ልቤም በተቀሠፈ ጊዜ፣

22ስሜት የሌለውና አላዋቂ ሆንሁ፤

በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ።

23ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፤

አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል።

24በምክርህ መራኸኝ፤

ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ።

25በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ?

በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም።

26ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤

እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣

የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው።

27እነሆ፤ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፤

አንተ ታማኞች ያልሆኑልህን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ።

28ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤

ጌታ እግዚአብሔርን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ፤

ስለ ሥራህም ሁሉ እናገር ዘንድ።