መዝሙር 55 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 55:1-23

መዝሙር 55

በስደት ጊዜ የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት ትምህርት55 ርእሱ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤

ልመናዬን ቸል አትበል፤

2ወደ እኔ ተመልከት፤ መልስልኝም።

በውስጤ ታውኬአለሁ፤ ተናውጬአለሁም፤

3በጠላት ድምፅ ተሸበርሁ፤

በክፉዎች ድንፋታ ደነገጥሁ፤

መከራ አምጥተውብኛልና፤

በቍጣም ተነሣሥተው ጠላት ሆነውብኛል።

4ልቤ በውስጤ ተጨነቀብኝ፤

የሞት ድንጋጤም በላዬ መጣ።

5ፍርሀትና እንቅጥቃጤ መጣብኝ፤

ሽብርም ዋጠኝ።

6እኔም እንዲህ አልሁ፤ “ምነው የርግብ ክንፍ በኖረኝ!

በርሬ በሄድሁና ባረፍሁ ነበር፤

7እነሆ፤ ኰብልዬ በራቅሁ፣

በምድረ በዳም በሰነበትሁ ነበር፤ ሴላ

8ከዐውሎ ነፋስና ከውሽንፍር ሸሽቼ፣

ወደ መጠለያዬ ፈጥኜ በደረስሁ ነበር።”

9ጌታ ሆይ፤ ግፍንና ሁከትን በከተማዪቱ ውስጥ አይቼአለሁና፣

ግራ አጋባቸው፤ ቋንቋቸውንም ደበላልቅ።

10ቀንና ሌሊት ቅጥሯ ላይ ወጥተው ይዞሯታል፤

ተንኰልና መከራ በውስጧ አለ።

11ጥፋት በመካከሏ ይገኛል፤

ግፍና አታላይነትም ከጎዳናዋ አይጠፋም።

12የሚዘልፈኝ ጠላት አይደለምና፤

ቢሆንማ ኖሮ በታገሥሁት ነበር፤

የሚጠላኝ፣ ራሱንም ቀና ቀና ያደረገብኝ ባላንጣ አይደለም፤

ቢሆንማ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።

13ነገር ግን አድራጊው አንተ ነህ፤ እኩያዬ፣ ባልንጀራዬና ወዳጄ፤

14በእግዚአብሔርም ቤት አብረን በሕዝብ መካከል ተመላለስን፤

ደስ የሚል ፍቅር በአንድነት ነበረን።

15ሞት ሳይታሰብ ድንገት ይምጣባቸው፤

በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል55፥15 ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል፤ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቅጆች ግን መቃብር ይላሉ። ይውረዱ፤

ክፋት በመካከላቸው ዐድራለችና።

16እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤

እግዚአብሔርም ያድነኛል።

17በማታ፣ በጧትና በቀትር፣

እጮኻለሁ፤ እቃትታለሁም፤

እርሱም ድምፄን ይሰማል።

18በተቃውሞ የተነሡብኝ ብዙዎች ናቸውና፣

ከተቃጣብኝ ጦርነት፣

ነፍሴን በሰላም ይቤዣታል።

19አካሄዳቸውን አልቀየሩምና፣

እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና፣

ከጥንት ጀምሮ በዙፋኑ ላይ ያለ አምላክ፣ ሴላ

ሰምቶ ያዋርዳቸዋል።

20ባልንጀራዬ የምለው ሰው እጁን

በወዳጆቹ ላይ ሰነዘረ፤

ቃል ኪዳኑንም አፈረሰ።

21አፉ ከቅቤ ይልቅ የለዘበ ነው፤

በልቡ ግን ጦርነት አለ፤

ቃሉ ከዘይት ይልቅ የለሰለሰ ነው፤

ይሁን እንጂ የተመዘዘ ሰይፍ ነው።

22የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤

እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤

የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።

23አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎችን ወደ ጥፋት ጕድጓድ

ታወርዳቸዋለህ፤

ደም የተጠሙ ሰዎችና አታላዮች፣

የዘመናቸውን እኩሌታ አይኖሩም።

እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ።