መዝሙር 142 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 142:1-7

መዝሙር 142

የሚታደን ሰው ጸሎት

ዋሻ ውስጥ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት፤142 ርእሱ ላይ ሥነ ጽሑፋዊ ወይም የዜማ ቃል ሊሆን ይችላል። ጸሎት።

1ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤

ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር ልመና አቀርባለሁ።

2ብሶቴን በፊቱ አፈስሳለሁ፤

ችግሬንም በፊቱ እናገራለሁ።

3መንፈሴ በውስጤ ሲዝል፣

መንገዴን የምታውቅ አንተ ነህ፤

በመተላለፊያ መንገዴ ላይ፣

ወጥመድ በስውር ዘርግተውብኛል።

4ወደ ቀኜ ተመልከት፤ እይም፤

ስለ እኔ የሚገድደው የለም፤

ማምለጫም የለኝም፤

ስለ ነፍሴም ደንታ ያለው የለም።

5እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤

ደግሞም፣ “አንተ መጠጊያዬ ነህ፤

በሕያዋንም ምድር ዕድል ፈንታዬ ነህ” እላለሁ።

6እጅግ ተስፋ ቈርጫለሁና፣

ጩኸቴን ስማ፤

ከዐቅም በላይ ሆነውብኛልና፣

ከሚያሳድዱኝ አድነኝ።

7ስምህን አመሰግን ዘንድ፣ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤

ከምታደርግልኝም በጎ ነገር የተነሣ፣

ጻድቃን በዙሪያዬ ይሰበሰባሉ።