መዝሙር 111 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 111:1-10

መዝሙር 111111 የግጥሙ መሥመሮች እያንዳንዳቸው ከላይ እስከ ታች በተከታታይ በዕብራይስጥ ፊደሎች ቅደም ተከተል የተቀመጡ ናቸው።

ለመለኮቱ ባሕርያት የቀረበ ጸሎት

1ሃሌ ሉያ።

በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣

ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።

2የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፤

ደስ የሚሰኙባትም ሁሉ ያውጠነጥኗታል።

3ሥራው ባለ ክብርና ባለ ግርማ ነው፤

ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

4ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤

እግዚአብሔር ቸር፣ ርኅሩኅም ነው።

5ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤

ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።

6ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣

የአሠራሩን ብርታት አሳይቷል።

7የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤

ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤

8ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤

በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው።

9ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤

ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤

ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።

10እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤

ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤

ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።