መዝሙር 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 11:1-7

መዝሙር 11

የጻድቃን ትምክሕት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤

ታዲያ ነፍሴን፣ “እንደ ወፍ ወደ ተራራ ብረሪ”

ለምን ትሏታላችሁ?

2ደግሞም ለምን እንዲህ ትሉኛላችሁ?

“ክፉዎች፣ እነሆ፤ ቀስታቸውን ገትረዋል፤

የቅኑን ሰው ልብ በጨለማ ለመንደፍ፣

ፍላጻቸውን በአውታሩ ላይ ደግነዋል።

3መሠረቱ ከተናደ፣

ጻድቅ ምን ማድረግ ይችላል?”11፥3 ወይም ጻድቁ ምን እያደረገ ነው?

4እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤

የእግዚአብሔር ዙፋን በሰማይ ነው።

ዐይኖቹ ሰዎችን ይመለከታሉ፤

ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።

5እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤11፥5 ወይም ጻድቁ እግዚአብሔር ኀጥኡን ይመረምራል

ዐመፃን የሚወድዱትን ግን፣

ነፍሱ ትጠላቸዋለች።

6እርሱ በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምና ዲን ያዘንባል፤

የጽዋቸውም ዕጣ ፈንታ፣

የሚለበልብ ዐውሎ ነፋስ ነው።

7እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፤

የጽድቅ ሥራም ይወድዳል፤

ቅኖችም ፊቱን ያያሉ።