መዝሙር 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 10:1-18

መዝሙር 1010 መዝ 9 እና 10 በመጀመሪያው የጥንት ቅጅ ላይ አንጓዎች ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምሩ እንዲሁም ጅማሬው ወይም መጨረሻው ትርጕም ዐዘል የሆነ አንድ ወጥ ግጥም ነበር በሰብዓ ሊቃናት ውስጥ ሁለቱ አንድ መዝሙር ናቸው።

ለፍትሕ የቀረበ ልመና

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምን እንዲህ ርቀህ ቆምህ?

በመከራ ጊዜስ ለምን ድምፅህን አጠፋህ?

2ክፉዎች የተጨነቀውን በእብሪት ያሳድዳሉ፤

በወጠኑት ተንኰል ይጠመዱ።

3ክፉ ሰው በልቡ ምኞት ይኵራራል፤

ስግብግቡን ይባርካል፤ እግዚአብሔርንም ይዳፈራል።

4ክፉ ሰው ከትዕቢቱ የተነሣ እግዚአብሔርን አይፈልግም፤

በሐሳቡም ሁሉ አምላክ የለም፤

5መንገዱ ዘወትር የተሳካ ነው፤

ዕቡይ፣ ከሕግህም የራቀ ነው።

በመሆኑም በጠላቶቹ ላይ ያፌዛል።

6በልቡም፣ “ከስፍራዬ የሚነቀንቀኝ የለም፤

ከትውልድ እስከ ትውልድም መከራ አያገኘኝም” ይላል።

7አፉ መርገምን፣ ቅጥፈትንና ግፍን የተሞላ ነው፤

ሽንገላና ክፋት ከምላሱ ሥር ይገኛሉ።

8በየመንደሩ ሥርቻ ያደፍጣል፤

ንጹሓንን በሰዋራ ስፍራ ይገድላል።

ዐይኖቹንም በምስኪኖች ላይ ያነጣጥራል።

9በደኑ ውስጥ እንዳለ አንበሳ በስውር ያደባል፤

ረዳት የሌለውን ለመያዝ ያሸምቃል፤

ድኻውንም አፈፍ አድርጎ በወጥመዱ ይጐትታል።

10ምስኪኑም ይደቅቃል፤ ዐንገቱን ይደፋል፤

ያልታደለውም በክንዱ ሥር ይወድቃል።

11በልቡም፣ “እግዚአብሔር ረስቷል፤

ፊቱን ሸፍኗል፤ ፈጽሞም አያይም”

ይላል።

12እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ አምላክ ሆይ፤ ክንድህን አንሣ፤

ረዳት የሌላቸውንም አትርሳ።

13ክፉ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ለምን ክፉ ይናገራል?

በልቡስ፣ “ስለ ሥራዬ አይጠይቀኝም”

ለምን ይላል?

14አንተ ግን መከራንና ሐዘንን ታያለህ፤

በእጅህም ዋጋ ለመክፈል ትመለከታለህ፤

ምስኪኑም ራሱን በአንተ ላይ ይጥላል፤

ለድኻ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።

15የክፉውንና የበደለኛውን ክንድ ስበር፤

የእጁንም ስጠው፤

ምንም እስከማይገኝ ድረስ።

16እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው፤

ሕዝቦችም ከምድሩ ይጠፋሉ።

17እግዚአብሔር ሆይ፤ የተገፉትን ምኞት ትሰማለህ፤

ልባቸውን ታበረታለህ፤ ጆሮህንም ወደ እነርሱ ጣል ታደርጋለህ፤

18ከዐፈር የተፈጠረ ሰው ከእንግዲህ

እንዳያስጨንቃቸው፣

አንተ ለድኻ ዐደጉና ለተገፋው ትሟገታለህ።