መሳፍንት 21 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መሳፍንት 21:1-25

ለብንያማውያን ሚስት ስለ ማግኘት

1እስራኤላውያን በምጽጳ፣ “ከእኛ አንድም ሰው ሴት ልጁን በጋብቻ ለብንያማውያን መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር።

2ሕዝቡ ወደ ቤቴል21፥2 ወይም ወደ እግዚአብሔር ቤት ተብሎ መተርጐም ይቻላል። ሄደው በዚያም እስከ ማታ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ አምርረው አለቀሱ፤ 3እንዲህም አሉ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ ለምን በእስራኤል ላይ ሆነ? ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዴት ይታጣ?”

4በማግስቱም ጧት ሕዝቡ መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት21፥4 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። አቀረቡ።

5በምጽጳ፣ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ያልተገኘ ማንኛውም ሰው መገደል አለበት ብለው እስራኤላውያን ተማምለው ስለ ነበር፣ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን አለ?” ሲሉ ጠየቁ።

6በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያማውያን በማዘን እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ታጥቷል፤ 7ሴቶች ልጆቻችንን ለእነዚህ ብንያማውያን በጋብቻ ላንሰጥ በእግዚአብሔር ስለ ማልን ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝላቸው እንችላለን?” 8ከዚያም፣ “ከእስራኤል ነገዶች ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን ነው” ሲሉ ጠየቁ፤ ታዲያ ከኢያቢስ ገለዓድ አንድም ሰው ለጉባኤው ወደ ሰፈሩ አለመምጣቱን ተረዱ፤ 9ሕዝቡን ሲቈጥሩም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች አንድም ሰው አልነበረምና።

10ስለዚህ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ተዋጊዎች ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሄደው በእዚያ የሚኖሩትን በሙሉ ሴቶቹንና ሕፃናቱን ጭምር በሰይፍ እንዲፈጇቸው ጉባኤው መመሪያ ሰጥቶ ላካቸው። 11እነርሱም፣ “እንግዲህ የምታደርጉት ይህ ነው፤ ወንዱን በሙሉ እንዲሁም ድንግል ያልሆኑትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ” አሏቸው። 12በኢያቢስ ገለዓድ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ወንድ ያልደረሰባቸው አራት መቶ ደናግል አገኙ፤ በከነዓን ምድር በሴሎ ወደሚገኘውም ሰፈር አመጧቸው።

13ከዚያም ጉባኤው በሙሉ በሬሞን ዐለት ወዳሉት ብንያማውያን የሰላም ጥሪ አስተላለፈ። 14ስለዚህ በዚህን ጊዜ ብንያማውያን ተመለሱ፤ ከመገደል የተረፉትንም የኢያቢስ ገለዓድ ሴቶች ሰጧቸው፤ ይሁን እንጂ የሴቶቹ ቍጥር ለሁሉም የሚበቃ አልነበረም። 15እግዚአብሔር በእስራኤል ነገዶች መካከል አስደንጋጭ ስብራት ስላደረገ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለብንያማውያን ዐዘነ። 16የጉባኤውም መሪዎች እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ የብንያም ሴቶች ዐልቀዋል፤ ታዲያ ለቀሩት ወንዶች ሚስት የምናገኝላቸው እንዴት ነው? 17ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው እንዳይጠፋ አሁን በሕይወት ያሉት ብንያማውያን ወራሽ የሚሆን ዘር ሊኖራቸው ይገባል። 18‘ልጁን ለብንያማዊ የሚድር ርጉም ይሁን’ ብለን እኛ እስራኤላውያን ስለ ተማማልን እንግዲህ ልጆቻችንን ልንድርላቸው አንችልም፤ 19ይሁን እንጂ ከቤቴል በስተ ሰሜንና ከቤቴል ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በስተ ምሥራቅ እንዲሁም ከለቦና በስተ ደቡብ ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ ይከበራል።”

20ስለዚህም ለብንያማውያን እንዲህ ሲሉ መመሪያ ሰጧቸው፤ “ሄዳችሁ በወይኑ የአትክልት ስፍራ ተደበቁ፤ 21አድፍጣችሁ ተጠባበቁ። የሴሎ ልጃገረዶች ለጭፈራ ወደዚያ በሚወጡበት ጊዜ፣ ከወይኑ አትክልት ቦታ ወጥታችሁ ከልጃገረዶቹ ለየራሳችሁ ሚስት ጥለፉ፤ ወደ ብንያምም ምድር ሂዱ። 22አባቶቻቸውም ሆኑ ወንድሞቻቸው ቢቃወሙ፣ ‘በጦርነት ጊዜ ለእያንዳንዳቸው የሚሆኑ ሚስቶች ስላላገኘን ነውና እነርሱን በመርዳት ምሕረት አድርጉልን፤ እናንተም ደግሞ ልጆቻችሁን ፈቅዳችሁ ያልዳራችሁ በመሆናችሁ በደለኞች አትሆኑም’ እንላቸዋለን።”

23ብንያማውያን እንደ ተባሉት አደረጉ፤ ልጃገረዶቹ በሚጨፍሩበትም ጊዜ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እየጠለፈ ሚስት እንድትሆነው ይዞ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ርስታቸው ተመለሱ፤ ከተሞቻቸውንም አድሰው በዚያ ኖሩ።

24በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ያን ቦታ ትተው ወደየቤታቸው፣ ወደየርስታቸው፣ ወደየጐሣቸውና ወደየነገዳቸው ሄዱ።

25በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።