ሕዝቅኤል 48 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 48:1-35

የምድሪቱ አከፋፈል

1“ስማቸው የተዘረዘረው ነገዶች እነዚህ ናቸው፤

“በሰሜኑ ድንበር የዳን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የሔትሎንን መንገድ ተከትሎ እስከ ሐማት መተላለፊያ ይደርሳል። ሐጸርዔናንና ከሐማት ቀጥሎ ያለው የደማስቆ ሰሜናዊ ድንበር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ላለው ወሰኑ አንድ ክፍል ይሆናል።

2የአሴር ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የዳንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

3የንፍታሌም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የአሴርን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

4የምናሴ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የንፍታሌምን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

5የኤፍሬም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የምናሴን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

6የሮቤል ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የኤፍሬምን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

7የይሁዳ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የሮቤልን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

8“ይሁዳን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚያዋስነው ምድር ለመባ የሚቀርብ ድርሻ ይሆናል፤ ስፋቱም ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ነው፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያለውም ርዝመቱ፣ ከነገዶቹ ድርሻ እንደ አንዱ ሆኖ፣ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል።

9ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የዚህ መባ ርዝመት ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ሲሆን፣ ስፋቱ ዐሥር ሺሕ ክንድ ይሆናል። 10ይህ ለካህናቱ የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ፣ በምዕራብ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺሕ ክንድ በምሥራቅ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺሕ ክንድ ሲሆን፣ በደቡብ በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይቆማል። 11ይህም እስራኤላውያን በሳቱ ጊዜ፣ እንደ ሳቱት ሌዋውያን ሳይስቱ ለቀሩት፣ በታማኝነት ላገለገሉኝ ለተቀደሱት ካህናት ለሳዶቃውያን ይሆናል። 12የሌዋውያንን ምድር ከሚያዋስነው፣ ከምድሪቱ ቅዱስ ድርሻ እጅግ የተቀደሰው ድርሻ ለእነርሱ ልዩ ስጦታ ይሆናል።

13“ከካህናቱም ምድር ጐን ለጐን ሌዋውያኑ ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺሕ ክንድ ወርድ ያለው ይዞታ ይኖራቸዋል፤ ጠቅላላ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺሕ ክንድ ይሆናል። 14ከዚህ ላይ መሸጥ ወይም መለወጥ የለባቸውም። ይህ ከምድሪቱ ሁሉ ምርጥ ስለሆነ፣ ወደ ሌላ እጅ አይተላለፍም፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና።

15“አምስት ሺሕ ክንድ ወርድና ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ርዝመት ያለው የቀረው ቦታ ለከተማዪቱ የጋራ ጥቅም፣ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያ ይውላል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች፤ 16የከተማዪቱም መጠን በሰሜን አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ፣ በደቡብ አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ፣ በምሥራቅ አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ፣ የምዕራቡም እንዲሁ አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። 17የከተማዪቱ ከብት ማሰማሪያ ቦታ፣ በሰሜን ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በደቡብ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምሥራቅ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምዕራብም ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። 18ከዚህ የሚቀረው፣ የተቀደሰውን ክፍል የሚያዋስነውና በተጓዳኝ ያለው ቦታ በምሥራቅ ዐሥር ሺሕ ክንድ፣ በምዕራብ ዐሥር ሺሕ ክንድ ይሆናል። ምርቱም ለከተማዪቱ ሠራተኞች ምግብ ይሆናል። 19ምድሪቱን የሚያርሱ የከተማዪቱ ሠራተኞች ከሁሉም ነገዶች ይመጣሉ። 20አጠቃላይ ይዞታው በአራቱም ማእዘን እኩል ሲሆን፣ እያንዳንዱ ማእዘን ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ነው፤ ከከተማዪቱ ድርሻ ጋር የተቀደሰውን ክፍል ልዩ መባ በማድረግ ታስቀምጣላችሁ።

21“በተቀደሰው ድርሻና በከተማዪቱ ቦታ ግራና ቀኝ ያለው ቀሪ ቦታ፣ ለገዥው ይሆናል፤ ይህም ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ከሆነው ከተቀደሰው ቦታ አንሥቶ በምሥራቅ በኩል እስከ ምሥራቁ ወሰን ይዘልቃል፤ በምዕራቡም በኩል እንዲሁ ሃያ አምስት ሺሕ ክንድ ከሆነው ይዞታ አንሥቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ይዘልቃል። የየነገዱ ድርሻ ከሆነውም መሬት ጐን ለጐን የሚሄዱት ቦታዎች የገዥው ይሆናሉ። የተቀደሰው ቦታና መቅደሱ በመካከላቸው ይሆናሉ። 22ስለዚህ የሌዋውያኑ ይዞታና የከተማዪቱ ይዞታ ለገዥው በተሰጠው ቦታ መካከል ይሆናል፤ የገዥው ቦታም በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል ይሆናል።

23“የቀሩት ነገዶች ድርሻ እንደሚከተለው ይሆናል፤

“የብንያም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ይዘልቃል።

24የስምዖን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

25የይሳኮር ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

26የዛብሎን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የይሳኮርን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

27የጋድ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የዛብሎንን ግዛት ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

28የጋድ ደቡባዊ ወሰን ከታማር ደቡብ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውሆች ይደርሳል፤ የግብፅን ደረቅ ወንዝ ይዞ እስከ ታላቁ ባሕር48፥28 ሜድትራኒያንን ያመለክታል ይዘልቃል።

29“ ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ምድር ይህች ናት፤ ድርሻዎቻቸውም እነዚህ ናቸው” ይላል ጌታ እግዚአብሔር

የከተማዪቱ በሮች

30“ የከተማዪቱ መውጫ በሮች እነዚህ ናቸው፤

“ከሰሜን በኩል አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት ካለው በር አንሥቶ፣ 31የከተማዪቱ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይጠራሉ፤ በሰሜን በኩል ያሉት ሦስቱ በሮች የሮቤል ነገድ በር፣ የይሁዳ ነገድ በርና የሌዊ ነገድ በር ይሆናሉ።

32በምሥራቅ በኩል አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች ይኖራሉ፤ እነዚህም የዮሴፍ በር፣ የብንያም በርና የዳን በር ናቸው።

33በደቡብ በኩል አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች አሉ፤ እነዚህም የስምዖን በር፣ የይሳኮር በርና የዛብሎን በር ናቸው።

34በምዕራብ በኩል አራት ሺሕ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች ይኖራሉ፤ እነዚህም የጋድ በር፣ የአሴር በርና የንፍታሌም በር ናቸው።

35“ የከተማዪቱም ዙሪያ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ክንድ ይሆናል፤

“ የከተማዪቱ ስም፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ” ይሆናል።