ሕዝቅኤል 44 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 44:1-31

ገዥው፣ ሌዋውያኑ፣ ካህናቱ

1ከዚያም ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በስተ ውጩ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መልሶ አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር። 2እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በር እንደ ተዘጋ ይኖራል፤ መከፈት የለበትም፤ ማንም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና፤ ተዘግቶ ይኖራል። 3በእግዚአብሔር ፊት ይበላ ዘንድ በመግቢያው በር ገብቶ ውስጥ ሊቀመጥ የሚችለው ገዥው ራሱ ብቻ ነው፤ በመግቢያው መተላለፊያ በረንዳ እንደ ገባ መውጣትም የሚችለው በዚያው ነው።”

4ከዚያም ያ ሰው በሰሜኑ በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አመጣኝ፤ እኔም ተመለከትሁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞልቶት አየሁ፤ በግንባሬም ተደፋሁ።

5እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥርዐት የምነግርህን ሁሉ በጥንቃቄ አስተውል፤ በሚገባ አድምጥ፤ ልብም በለው። የቤተ መቅደሱን መግቢያና የመቅደሱን መውጫዎች ሁሉ አስተውል፤ 6ለዐመፀኛው የእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አስጸያፊ ሥራችሁ ከእንግዲህ ያብቃ! 7ከአስጸያፊ ሥራችሁም ሌላ ምግብ፣ ሥብና ደም ስታቀርቡ ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙትን እንግዶች ወደ መቅደሴ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አረከሳችሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አፈረሳችሁ። 8እናንተ ራሳችሁ ማድረግ የሚገባችሁን ቅዱሳት ሥርዐቶቼን በመፈጸም ፈንታ ባዕዳንን በኀላፊነት በመቅደሴ አስቀመጣችሁ። 9ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ ባዕድ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ቢሆንም እንኳ ወደ መቅደሴ አይግባ።

10“ ‘እስራኤል እኔን ከመከተል በራቁ ጊዜ፣ ከእኔ የራቁትና ጣዖቶቻቸውን በመከተል የተቅበዘበዙት ሌዋውያን የኀጢአታቸውን ዕዳ ይሸከማሉ። 11የቤተ መቅደሱ በር ኀላፊ በመሆንና በእርሱም ውስጥ በማገልገል፣ መቅደሴን ሊያገለግሉ ይችላሉ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዐርደው ስለ ሕዝቡ ሊሠዉ፣ በፊታቸው ሊቆሙና ሊያገለግሏቸው ይችላሉ። 12ነገር ግን ሕዝቡን በጣዖቶቻቸው ፊት ስላገለገሏቸውና የእስራኤል ቤት በኀጢአት እንዲወድቅ ስላደረጉ፣ ስለዚህ የኀጢአታቸውን ዋጋ መቀበል እንዳለባቸው እጄን አንሥቼ ምያለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር13እንደ ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፤ ወይም ቅዱስ ወደ ሆነው ነገሬ ሁሉ፣ ወይም እጅግ ወደ ተቀደሱ መሥዋዕቶቼ አይቀርቡም፤ የአስጸያፊ ድርጊታቸውን ኀፍረት ይሸከማሉ። 14ያም ሆኖ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲሠሩ፣ በውስጡ የሚከናወኑትንም ሥራዎች ሁሉ እንዲቈጣጠሩ አደርጋቸዋለሁ።

15“ ‘ነገር ግን እስራኤላውያን ከመንገዴ ስተው በወጡ ጊዜ፣ የመቅደሴን ሥራ በታማኝነት ያከናወኑት የሳዶቅ ዘርና ሌዋውያን የሆኑት፣ በፊቴ ቀርበው ያገለግሉኛል፤ በፊቴ ቆመው የሥብና የደም መሥዋዕት ያቀርቡልኛል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር16እነርሱ ብቻ ወደ መቅደሴ ይገባሉ፤ እነርሱ ብቻ በፊቴ ሊያገለግሉ፣ ሥርዐቴንም ሊፈጽሙና ወደ ገበታዬ ሊቀርቡ ይችላሉ።

17“ ‘ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሮች ሲገቡ፣ የበፍታ ፈትል ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በሮችም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያገለግሉ፣ ከበግ ጠጕር የተሠራ ልብስ አይልበሱ። 18በራሳቸው ላይ ከበፍታ ፈትል የተሠራ ጥምጥም ያድርጉ፤ እንዲሁም ከበፍታ ፈትል የተሠራ ሱሪ በወገባቸው ላይ ይታጠቁ፤ እንዲያልባቸው የሚያደርግ ማንኛውንም ልብስ አይልበሱ። 19ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ውጩ አደባባይ ሲወጡ፣ ሲያገለግሉበት የነበረውን ልብስ አውልቀው በተቀደሱት ክፍሎች በመተው ሌሎች ልብሶችን ይልበሱ፤ ይኸውም ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ነው።

20“ ‘የራሳቸውን ጠጕር አይላጩት፤ ወይም አያርዝሙት፤ ነገር ግን ይከርክሙት። 21ማንኛውም ካህን ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጣ። 22መበለቶችን ወይም ፈት ሴቶችን አያግቡ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ዘር የሆኑ ድንግሎችን ወይም የካህናት ሚስቶች የነበሩትን መበለቶች ማግባት ይችላሉ። 23በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ያለውን ልዩነት ለሕዝቤ ያስተምሩ፤ የረከሰውንና ያልረከሰውን እንዴት እንደሚለዩም ያሳዩአቸው።

24“ ‘በማንኛውም ክርክር ካህናት ዳኞች ሆነው ያገልግሉ፤ በሥርዐቴም መሠረት ይወስኑ። የተለዩ በዓላቴን የሚመለከቱ ሕጎቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ ይጠብቁ፤ ሰንበታቴንም ቅዱስ አድርገው ይጠብቁ።

25“ ‘ካህን ወደ ሞተ ሰው ሬሳ በመጠጋት ራሱን አያርክስ፤ ይሁን እንጂ ሟች አባቱ ወይም እናቱ፣ ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ፣ ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ብትሆን፣ ራሱን ማርከስ ይችላል። 26ከነጻም በኋላ፣ ሰባት ቀን መቈየት አለበት። 27በመቅደሱ ለማገልገል፣ ወደ መቅደሱ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ቀን፣ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

28“ ‘ለካህናቱ ርስታቸው እኔ ብቻ ነኝ፤ በእስራኤል ምንም ዐይነት ርስት አትስጧቸው፤ እኔ ርስታቸው እሆናለሁ። 29የእህሉን ቍርባን፣ የኀጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤል ለእግዚአብሔር የተሰጠው44፥29 የዕብራይስጡ ቃል ዕቃዎችን ወይም ሰዎችን ለእግዚአብሔር ከመስጠት አኳያ የማይለወጥ መደበኛ መስጠትን ያመለክታል። ሁሉ የእነርሱ ይሆናል። 30ከፍሬ በኵራት ምርጥ የሆነው ሁሉ እንዲሁም ከልዩ ስጦታዎቻችሁ የመጀመሪያው ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ ለቤተ ሰዎቻችሁ ሁሉ በረከት እንዲሆን ከምድር የምታገኙትን መብል በኵራት ለእነርሱ ስጧቸው። 31ካህናት ሞቶ የተገኘውን ወይም በዱር አራዊት የተዘነጠለውን ወፍም ይሁን ሌላ እንስሳ፣ ማንኛውንም ነገር መብላት የለባቸውም።’ ”