ሕዝቅኤል 43 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 43:1-27

የእግዚአብሔር ክብር ወደ ቤተ መቅደሱ መመለስ

1ከዚያም ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በር አመጣኝ፤ 2እኔም የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ ድምፁ እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ነበር፤ ምድሪቱም ከክብሩ የተነሣ ታበራ ነበር። 3ያየሁትም ራእይ ከተማዪቱን ለማጥፋት በመጣ ጊዜ ያየሁትን ራእይ የሚመስልና እንዲሁም በኮቦር ወንዝ ካየሁት ራእይ ጋር የሚመሳሰል ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ። 4የእግዚአብሔር ክብር ለምሥራቅ ትይዩ በሆነው በር ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። 5ከዚያም መንፈስ አነሣኝ፤ ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው።

6ያ ሰው በአጠገቤ ቆሞ ሳለ፣ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲናገረኝ ሰማሁ፤ 7እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ የእግሬም ጫማ ማሳረፊያ ነው፤ በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም የምኖርበትም ስፍራ ነው። የእስራኤል ቤትም ሆኑ ነገሥታታቸው በአመንዝራነታቸውና43፥7 ወይም መንፈሳዊ ግልሙትናቸውን፤ እንዲሁም 9 በማምለኪያ ኰረብታቸው ላይ በሚያመልኳቸው፣ ሕይወት በሌላቸው በነገሥታታቸው ጣዖታት43፥7 ወይም ሬሳ፤ እንዲሁም 9 ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም። 8በእኔና በጣዖታቱ መካከል ግንብ ብቻ ሲቀር፣ መድረኮቻቸውን ከመድረኬ አጠገብ፣ መቃኖቻቸውን ከመቃኖቼ አጠገብ በማድረግ፣ በአጸያፊ ድርጊታቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው። 9ከእንግዲህ አመንዝራነታቸውንና ሕይወት የሌላቸውን የንጉሦቻቸውን ጣዖታት ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።

10“የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ኀጢአታቸው ያፍሩ ዘንድ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ቤተ መቅደሱን አሳያቸው፤ ንድፉንም ያስተውሉ፤ 11ስላደረጉት ነገር ሁሉ ኀፍረት የሚሰማቸው ከሆነ፣ የቤተ መቅደሱን ንድፍ እንዲያውቁት አድርግ፤ ይኸውም አሠራሩን፣ መውጫና መግቢያውን፣ አጠቃላይ ንድፉን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ43፥11 አንዳንድ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆችና ሰብዐ ሊቃናት እንዲሁ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ግን ሥርዓቶቹንና የራሱን ንድፎች ሁሉ ይላሉ ነው። ንድፉንና ሥርዐቱን እንዲጠብቁና እንዲከተሉ እነዚህን ሁሉ እነርሱ ባሉበት ጻፋቸው።

12“የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ አካባቢ ያለው ስፍራ ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። የቤተ መቅደሱም ሕግ ይኸው ነው።

የቤተ መቅደሱ መሠዊያ

13“የመሠዊያው ልክ በረዥም ክንድ ይህ ነው፤ ይኸውም ክንድ ከስንዝር ማለት ነው፤ ቦዩ አንድ ክንድ ጥልቀት፣ አንድ ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ዙሪያው አንድ ስንዝር ጠርዝ አለው፤ የመሠዊያውም ከፍታ ይህ ነው፤ 14ከቦዩ መሠረት አንሥቶ እስከ ታችኛው ዕርከን ድረስ ሁለት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ከትንሹ ዕርከን አንሥቶ እስከ ትልቁ ዕርከን ድረስ ደግሞ አራት ክንድ ቁመት፣ አንድ ክንድ ወርድ አለው። 15የመሠዊያው ምድጃ ከፍታው አራት ክንድ ሲሆን፣ ከምድጃው ወጣ ወጣ ያሉ አራት ቀንዶች አሉ። 16የመሠዊያው ምድጃ እኩል በእኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ክንድ፣ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው። 17ላይኛው ዕርከንም እንዲሁ እኩል በእኩል ሆኖ ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ አለው፤ ግማሽ ክንድ ጠርዝና ዙሪያውን በሙሉ አንድ ክንድ የሆነ ቦይ ነበረው። የመሠዊያው ደረጃዎችም በምሥራቅ ትይዩ ናቸው።”

18ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መሠዊያው ተሠርቶ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚሠዋበትና በመሠዊያው ላይ ደም በሚረጭበት ጊዜ ሥርዐቶቹ እነዚህ ናቸው፤” 19በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር20ከደሙም ጥቂት ወስደህ፣ በመሠዊያው አራት ቀንዶች፣ በላይኛው ዕርከን አራት ጐኖች ላይ እንዲሁም በጠርዙ ዙሪያ ሁሉ ታደርጋለህ፤ በዚህ ሁኔታ መሠዊያውን ታነጻለህ፤ ታስተሰርይለታለህም። 21ወይፈኑን ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወስደህ፣ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ከመቅደሱ ውጩ ለዚሁ ተብሎ በተመደበው ስፍራ ታቃጥለዋለህ።

22“በሁለተኛው ቀን እንከን የሌለበት ተባት ፍየል ወስደህ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባለህ፤ መሠዊያው በወይፈኑ እንደ ነጻ ሁሉ፣ በዚህም መንጻት አለበት። 23ማንጻቱን ከፈጸምህ በኋላ፣ ከመንጋው እንከን የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ ታቀርባለህ። 24በእግዚአብሔር ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱ ጨው ይነሰንሱባቸዋል፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቧቸዋል።

25“በየዕለቱ ለሰባት ቀን ተባት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባለህ፤ 26ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርዩለታል፤ ያነጹታልም፤ እንዲህም አድርገው ይቀድሱታል። 27እነዚህ ቀኖች ካለፉ በኋላም፣ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁንና የኅብረት መሥዋዕታችሁን43፥27 በትውፊት የድነት መሥዋዕት ይባላል። በመሠዊያው ላይ ያቀርባሉ። ከዚያም እኔ እቀበላችኋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”