ሕዝቅኤል 24 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 24:1-27

የድስቱ ምሳሌ

1በዘጠነኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ቀን፣ የዛሬውን ዕለት፣ ለይተህ መዝግብ፤ የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በዚህ ቀን ከብቧታልና። 3ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ ብለህ ተምሳሌት ተናገር፤ ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ብረት ድስት በእሳት ላይ ጣድ፤

ከጣድህም በኋላ ውሃ ጨምርበት።

4ሙዳ፣ ሙዳ ሥጋ፣

ምርጥ ምርጡን ቍርጥ ሁሉ፣ ጭንና ወርቹን ጨምርበት፤

የተመረጡ ዐጥንቶችንም ሙላበት።

5ከመንጋው ሙክቱን ውሰድ፤

ዐጥንቱን ለማብሰል ብዙ ማገዶ ከሥሩ ጨምር፤

ሙክክ እስከሚል ቀቅለው፤

ዐጥንቱም ይብሰል።

6“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤

“ ‘ለዛገችው ብረት ድስት

ዝገቷም ለማይለቅ፣

ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት!

መለያ ዕጣ ሳትጥል

አንድ በአንድ አውጥተህ ባዶ አድርገው።

7“ ‘የሰው ደም በመካከሏ አለ፤

በገላጣ ዐለት ላይ አደረገችው እንጂ፣

ዐፈር ሊሸፍነው በሚችል፣

በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም።

8ቍጣዬ እንዲነድድና ለመበቀል እንዲያመቸኝ፣

ይሸፈንም ዘንድ እንዳይችል፣

ደሟን በገላጣ ዐለት ላይ አፈሰስሁ።

9“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት!

እኔም ደግሞ የምትቃጠልበትን ማገዶ እቈልላለሁ።

10ማገዶውን ከምርበት፤

እሳቱን አንድድ፤

ቅመም ጨምረህበት፣

ሥጋውን በሚገባ ቀቅል፤

ዐጥንቱም ይረር።

11ጕድፉ እንዲቀልጥ፣

ዝገቱም በእሳት እንዲበላ፣

ባዶው ድስት እስኪሞቅ፣

መደቡም እስኪግል ከሰል ላይ ጣደው።

12ብዙ ጕልበት ቢፈስስበትም፣

የዝገቱ ክምር፣

በእሳት እንኳ፣ ሊለቅ አልቻለም።

13“ ‘የረከስሽው በብልግናሽ ነው፤ ቍጣዬ በአንቺ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ ንጹሕ አትሆኚም፤ ከርኩሰትሽ ላነጻሽ ፈልጌ፣ መንጻት አልወደድሽምና።

14“ ‘እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ የምሠራበትም ጊዜ ደርሷል፤ ወደ ኋላ አልልም፤ አልራራም፤ አላመነታምም። እንደ መንገድሽና እንደ ተግባርሽ ይፈረድብሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

የሕዝቅኤል ሚስት መሞት

15የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 16“የሰው ልጅ ሆይ፤ የዐይንህ ማረፊያ የሆነውን ነገር በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተ ግን ዋይታ አታሰማ፤ አታልቅስ፤ እንባህንም አታፍስስ፤ 17ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በሐዘን አንጐራጕር እንጂ ለሞተው አታልቅስ። ጥምጥምህን ከራስህ አታውርድ፤ ጫማህንም አታውልቅ፤ አፍህ ድረስ አትሸፋፈን፤ የዕዝን እንጀራም አትብላ።”

18እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ሚስቴም ማታውኑ ሞተች፤ በማግስቱም ጧት እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19ሕዝቡም፣ “ይህን ስታደርግ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ።

20እኔም እንዲህ አልኋቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 21ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 22እኔ እንዳደረግሁም ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁ ድረስ አትሸፋፈኑም፤ የዕዝን እንጀራም አትበሉም፤ 23ጥምጥማችሁን ከራሳችሁ አታወርዱም፤ ጫማችሁንም አታወልቁም። በኀጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርስ ታቃስታላችሁ እንጂ ሐዘን አትቀመጡም፤ አታለቅሱምም። 24ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገው ታደርጋላችሁ፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’

25“አንተም የሰው ልጅ ሆይ፤ ኀይላቸውን፣ ደስታቸውንና፣ ክብራቸውን፣ የዐይናቸው ማረፊያና የልባቸው ደስታ የሆኑትን ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ጭምር በምወስድባቸው ቀን፣ 26በዚያን ቀን፣ ያመለጠ ሰው ይህን ወሬ ሊነግርህ ወደ አንተ ይመጣል፤ 27በዚያን ቀን አፍህ ተከፍቶ ከእርሱ ጋር ትነጋገራለህ፤ ከዚያም በኋላ እንደ ድዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”