ሐዋርያት ሥራ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሐዋርያት ሥራ 2:1-47

በበዓለ አምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወረደ

1የበዓለ አምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር። 2ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው። 3የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። 4ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች2፥4 ወይም ልሳኖች እንዲሁም በ11 ይናገሩ ጀመር።

5በዚህ ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ። 6ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤ 7በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? 8ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድንበት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው? 9እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጰዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣ 10በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን 11አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!” 12ሁሉም በአድናቆትና ግራ በመጋባት፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።

13አንዳንዶቹ ደግሞ “ያልፈላ ብዙ የወይን ጠጅ2፥13 ወይም ጣፋጭ ወይን ጠጥተዋል” በማለት አፌዙባቸው።

ጴጥሮስ ለሕዝቡ ንግግር አደረገ

14በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንት የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ። 15ጊዜው ገና ከጧቱ ሦስት ሰዓት ስለሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም። 16ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤

17“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣

መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤

ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤

ጕልማሶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤

ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ።

18በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ፣

መንፈሴን አፈስሳለሁ፤

እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።

19በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣

አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤

ደምና እሳት፣ የጢስም ጭጋግ ይሆናል።

20ታላቅና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣

ፀሓይ ወደ ጨለማ፣

ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

21የጌታን ስም፣

የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’

22“የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንት ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል። 23እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች2፥23 ወይም ሕግ በሌላቸው ሰዎች (አሕዛብን ያመለክታል) እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። 24እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና። 25ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤

“ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤

እርሱ በቀኜ ነውና፣

ከቶ አልታወክም።

26ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤

ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል።

27ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤

ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አታደርግም።

28የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤

በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’

29“ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ። 30ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ። 31ይህን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም እንደማይበሰብስ ስለ ክርስቶስ2፥31 ወይም መሲሕ፤ በግሪኩ ክርስቶስ፣ በዕብራይስጡ መሲሕ የሁለቱም ቃላት ትርጕም የተቀባው ማለት ነው፤ እንዲሁም በ36 ትንሣኤ ተናገረ። 32ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። 33ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም፤ እርሱ ራሱ ግን እንዲህ ብሏል፤

“ ‘ጌታ ጌታዬን፣

35“ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣

እስከማደርግልህ ድረስ፣

በቀኜ ተቀመጥ” አለው።’

36“እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን፣ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ!”

37ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” አሏቸው።

38ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። 39የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።”

40በሌላ ብዙ ቃል እየመሰከረላቸው፣ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለት አስጠነቀቃቸው። 41ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ፤ በዚያ ቀን ሦስት ሺሕ ያህል ሰዎች በቍጥራቸው ላይ ተጨመሩ።

የአማኞች የኅብረት ኑሮ

42እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር። 43በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ታምራት ይደረግ ስለ ነበር፣ ሰው ሁሉ ፍርሀት ዐደረበት። 44ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ። 45ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር። 46በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤ 47እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።