ሉቃስ 20 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሉቃስ 20:1-47

የኢየሱስ ሥልጣን ለአይሁድ አጠያያቂ ሆነባቸው

20፥1-8 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥23-27ማር 11፥27-33

1አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ። 2እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደ ሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ለመሆኑ እርሱ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።

3እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስቲ መልሱልኝ፤ 4የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?”

5እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ 6‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።”

7ስለዚህ፣ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት።

8ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

የጭሰኞቹ ምሳሌ

20፥9-19 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥33-46ማር 12፥1-12

9ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ። 10በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት አገልጋዩን ወደ እነዚህ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት። 11ቀጥሎም ሌላ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት። 12አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቍስለው ወደ ውጭ ጣሉት።

13“የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስቲ ደግሞ የምወድደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ።

14“ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤ 15ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት።

“እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል? 16መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።”

ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ።

17ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤

“ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

እርሱ የማእዘን ራስ20፥17 ወይም የማእዘን ድንጋይ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጕሙ ምንድን ነው?

18በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቅቃል።”

19ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያኑ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።

ለቄሣር ግብር መክፈል

20፥20-26 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥15-22ማር 12፥13-17

20ኢየሱስን አሳልፈው ለገዥው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። 21ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። 22ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

23እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ 24“እስቲ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?”

25እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት።

እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።

26ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።

ትንሣኤ ሙታንና ጋብቻ

20፥27-40 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥23-33ማር 12፥18-27

27ትንሣኤ ሙታን የለም ከሚሉት ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፤ 28እንዲህም አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ መበለቲቱን አግብቶ ልጆች በመውለድ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። 29ታዲያ፣ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ 30ሁለተኛውም እንደዚሁ፤ 31ሦስተኛው ደግሞ አገባት፤ ሰባቱም እንዲሁ እያሉ አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ። 32በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 33እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት፣ በትንሣኤ ጊዜ የማን ሚስት ትሆናለች?”

34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፤ ይጋባሉም፤ 35የሚመጣውን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ማግኘት የሚገባቸው ግን አያገቡም፤ አይጋቡም፤ 36እንደ መላእክትም ስለሆኑ ከዚያ በኋላ አይሞቱም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለ ሆኑም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 37ሙሴ ስለ ቍጥቋጦ በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ጌታን፣ ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ’ በማለቱ ሙታን እንደሚነሡ ያሳያል፤ 38ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም።”

39አንዳንድ ጸሐፍትም፣ “መምህር ሆይ፤ መልካም ተናገርህ” አሉት። 40ከዚህ በኋላ አንድ ሰው እንኳ ሊጠይቀው አልደፈረም።

ክርስቶስ የማን ልጅ ነው?

20፥41-47 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥41–23፥7ማር 12፥35-40

41ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ክርስቶስን20፥41 ወይም መሲሕ እንዴት የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል? 42ምክንያቱም ራሱ ዳዊት በመዝሙራት መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፤

“ ‘ጌታ ጌታዬን፣

“በቀኜ ተቀመጥ፤

43እኔ ጠላቶችህን፣

ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ።” ’

44እንግዲህ ዳዊት እርሱን፣ ‘ጌታ’ ብሎ ሲጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”

45ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙትም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤ 46“ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞር ከሚወድዱ፣ በገበያ ቦታ ሰላምታ ከሚሹና በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫ፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራ ከሚፈልጉ፣ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ 47እነርሱም የመበለቶችን ቤት የሚያራቍቱ ናቸው፤ ለታይታ ብለውም ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ፤ እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።”