ዘሌዋውያን 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘሌዋውያን 2:1-16

የእህል ቍርባን

1“ ‘ማንኛውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ዱቄቱ የላመ ይሁን፤ ዘይት ያፍስስበት፤ ዕጣንም ይጨምርበት፤ 2ወደ ካህናቱም ወደ አሮን ልጆች ያምጣው። ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ሙሉ ያንሣለት፤ ዕጣኑንም ሁሉ ይውሰደው፤ ይህንም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። 3የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።

4“ ‘በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ የእህል ቍርባን በምታቀርብበት ጊዜ፣ ከላመ ዱቄት ተዘጋጅቶ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ኅብስት ይሁን፤ አለዚያም2፥4 ወይም እንዲሁም ያለ እርሾ በስሱ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ ይሁን። 5የእህል ቍርባንህ በምጣድ የሚጋገር ከሆነ፣ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ከተለወሰ ከላመ ዱቄት ይዘጋጅ። 6ቈራርሰህ ዘይት አፍስስበት፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 7የእህል ቍርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ። 8በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤ 9ከእህሉም ቍርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10የተረፈውም ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።

11“ ‘ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት በምታቀርቡት ቍርባን ውስጥ እርሾ ወይም ማር ጨምራችሁ ማቃጠል ስለማይገባችሁ፣ በምታቀርቡት በማንኛውም የእህል ቍርባን እርሾ አይኑርበት። 12እነዚህን የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሽታው ደስ የሚያሰኝ ቍርባን ሆነው በመሠዊያ ላይ ለመቃጠል አይቀርቡም። 13የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ቀምመው፤ የአምላክህ (ኤሎሂም) የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አይታጣ፤ በቍርባንህም ላይ ጨው ጨምርበት።

14“ ‘የእህል በኵራት ቍርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታመጣበት ጊዜ፣ የተፈተገና በእሳት የተጠበሰ እሸት አቅርብ። 15ዘይት ጨምርበት፤ ዕጣንም በላዩ አስቀምጥ፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 16ካህኑም ከተፈተገው እህልና ከዘይቱ ወስዶ፣ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መታሰቢያ አድርጎ ያቃጥል።